








የ2017 የካፈቾ የአዲስ ዘመን መለወጫ (ማሽቃሮ) በቦንጋ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የነገስታት መነገሻ ስፍራ ‹‹ቦንጌ ሻምበቶ›› በድምቀት ተከብሯል።
የካፈቾዎች የአዲስ ዘመን (ማሽቃሮ) በዓል ከ1897 በፊት በደማቅ ህዝባዊ ተሳትፎ ይከበረ እንደነበረ ያወሱት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ይሁን እንጅ በሀገራችን የዲሞክራሲ ስርዓት እስከሰፍን 1990ዎቹ የበዓሉን አከባቢር ማስቀጠል አለመቻሉን ተናግረዋል።
የማሽቃሮ በዓል በ1986 በተካሄደው የመጀመሪያው የካፋ የቋንቋና ባህል ሲምፖዚየም ተወስኖ ከ1998 ጀምሮ በአዲስ መልክ መከበር ከጀመረ የዘንድሮው ለ20ኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁመዋል።
ካፋ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት በመሆን ለዘመናዊ የፖለቲካና የአስተዳደር ስረዓት መነሻ የሆነ የምክር ቤት አስተዳደር (ምክርቾ) ስርዓት ባለቤት መሆኑን ነው ዋና አስተዳዳሪው የገለጹት።
በካፈቾች ዘንድ ማሽቃሮ የአብሮነትና የመቻቻል ተምሳሌት ተደርጎ ይወስዳል ያሉት አቶ እንዳሻው በዚህም በተለያየ አከባቢ ያሉ ለበዓሉ የሚሰበሰቡበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት እና በአዲስ መንፈስ አከባቢያቸውን ለማልማት የሚመክሩበት እንደሆነም ነው የገለጹት።
ቀደምት የካፈቾዎች ንጉሥዊ የአስተዳደር ስረዓት ከበዓሉ አስቀድመው የግዛት አስተዳዳሪዎችን (ወራፌ ራሻዎችን) ወደ ንጉሡ በመጥራት ስለ አዝመራው ምርት እና ስለ አካባቢ ሠላምና ደህንነት የሚመክሩበት ሲሆን በዚህም የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ በምክርቾ ፊት እውቅናና ሹመት የሚሰጣቸው እንደሆነም ነው የገለጹት።
የካፋ ዞን ከቀደምት ታሪካዊና ባህላዊ ተውፊቶች ባሻገር በአለማችን የቡና መገኛ በመሆን ለአለም ቡና ያበረከት ለምለም ምድር መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው አቶ እንዳሻው ዞኑ ሶስቱ ብሔረሰቦች በሠላም ተዋደውና ተከባብረው የሚኖሩበት ሠላማዊ ቀጠና መሆኑን ተናግረዋል።
ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በድምቀት ስከበር የቆየውን የካፈቾዎች የአዲስ ዘመን የማሽቃሮ በዓል በመጠበቅና በማልማት በተባበሩት መንግሥት ድርጅት የማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ የተጀመረ እንቅስቃሴ መኖሩን ያመለከቱት አቶ እንዳሻው ይህንን ጅምር እንቅስቃሴ በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው አካላት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል።
የዞኑ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መመሪያ ኃላፊ አቶ ነጻነት ብርሀኑ በበኩላቸው የካፋ ዞን በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ፤ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ተጨማሪ ምንጭ የሚሆን የቱሪዝም ሀብትን በውስጡ ያካተተ እንደሆነ ተናግረዋል።
የዘንድሮው የማሽቃሮ በዓል በየደረጃው ባሉት የአስተዳደር መዋቅሮች በደማቅ ህዝባዊ ተሳትፎ ስከበር መቆየቱን የገለጹት አቶ ነጻነት በዓሉ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የብዝሀ ማንነቶች ባለቤት መሆኗን የገለጹት የዕለቱ ክብር እንግዳ የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ተወካይ አቶ ሞሲሳ ለሚ እነዚህን ህብር ማንነቶች ለማልማትና ለማሳደግ የሚያስችል የባህል ፖሊስ ተቀርጾ ስራ ላይ መዋሉን ገልጸዋል።
የማሽቃሮ ባህላዊና ታሪካዊ ዕሴት በማጉላት በሀገር አቀፍና አለማቀፍ መድረኮች ለማስተዋወቅ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የገለጹት አቶ ሞሲሳ ባህሉ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ያደረጉ የባህል ምክር ቤት አባላትና መላው የዞኑን ህዝብ አመስግነዋል።
የዘንድሮው የማሽቃሮ በዓል የቀደምት የካፋ ነገስታት መነገሻ በሆነው ‹‹ቦንጌ ሻምበቶ›› በልዩ ድምቀት በባህላዊ ክዋኔዎች ተከብሯል።
በበዓሉ የካፈቾ የባህል ምክር ቤት አባላት፣ የአከባቢው ተወላጆች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
