




በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የታርጫ ደንበኞች አገልግሎት ማዕከል ችግሩን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራዉ ነዉ ብሏል።
በዞኑ ታርጫ ከተማ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው የሚሠሩ ሲሳይ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች ማምረቻ ማህበር ዋና ሰብሳቢ አቶ ሲሳይ እሸቱ እንደገለጹት የመብራት አገግሎት መቆራረጥ በኢኮኖሚ ላይም ተጽዕኖ ከማሳደር ባለፈ የመልካም አስተዳደር አገልግሎት ጥያቄ እየሆነ ይገኛል ብለዋል።
ማህበሩ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው ያሉት አቶ ሲሳይ በማህበሩ ያሉ ማሽነሪዎች ከመብራት ኃይል ውጭ በሌላ አማራጭ የሚነሳ ባለመሆኑ የዕለት ተግባር ማከናወን አለመቻላቸውን ገልፀዋል።
በታርጫ ከተማ የሚገኘው ቃል ኪዳን የወንዶችና የሴቶች ልብስ ስፌት ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ባንችአምላክ አበራ በበኩላቸው የማህበሩ ሰራተኞች የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደገጠማቸው አብራርተዋል።
ከዚህም አልፎ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንበኞችን ፍላጎትና እርካታ ማረጋገጥ አለመቻላቸውን የማህበሩ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ሮ ባንችአምላክ እና አቶ ሲሳይ በጋራ በሰጡን አስተያየት ገልጸዋል።
የታርጫ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አሰፋ ዋጄቦ በበኩላቸዉ የመብራት አገልግሎት መቆራረጥ ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።
በከተማዋ እና አከባቢዋ የሚገኙ ለመብራት መስመር ዝርጋታ የቆሙ ፖሎች እድሜ ጠገብ በመሆናቸው በየጊዜው መውደቃቸው ለአገልግሎት መቋረጥ መንስኤ እንደሆነም ነው የገለጹት።
ካነጋገርናቸው የከተማው ነዎሪዎችም መካከል አንዳንዶች እንደሚሉት በየቦታው ያሉ የመብራት ፖሎች ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ በመሆናቸው ወደ ብረት እንዲቀየሩ አስተያየት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዳዉሮ ዞን ታርጫ ደንበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው አጋሮ እንደገለጹት የመብራት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማሻሻል እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የሆኑ አደጋዎች ለመብራት አገልግሎት መቆራረጥ ሁነኛ መንስኤ መሆናቸዉን ገልጸዋል ።
በቀጣይ የሚታየውን ማነቆ በዘለቂነት ለመፍታት እንዲቻል በዝናብ ምክንያት የሚሰነጠቁ ሲኒና መስመሮችን የመለየትና በኤሌክትሪክ መስመሮች ሥር ያሉ የትኛውንም ፀዳቂ ዛፎችን ከመስመሩ ግራና ቀኝ እስከ 3 ሜትር መንጥሮ የማስወገድ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ነው የገለፁት።
የተለያዩ ሰው ሰራሽ አደጋዎች በማድረስ ለመቆራረጥ ምክንያት የሚሆኑ ግለሰቦችን በመጠቆም የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ እና የህግ የበላይነት በማስከበር የአካባቢው ማህበረሰብ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የባለድርሻ አካላት በመቀናጀት ለዘላቂ መፍትሔ የጋራ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
