በክልሉ ለ2018 ትምህርት ዘመን ከ1.2 ሚልዮን በላይ መፅሀፍት ታትመው ለተማሪዎች እንዲደርስ

Spread the love

በክልሉ ለ2018 ትምህርት ዘመን ከ1.2 ሚልዮን በላይ መፅሀፍት ታትመው ለተማሪዎች እንዲደርስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የ2018 የትምህርት ዘመን ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አልማው ዘውዴ ገልፀዋል።

የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የትምህርት ግብአቶችን ማሟላት ወሳኝ መሆኑን ያብራሩት አቶ አልማው በዚህም ለ2018 የትምህርት ዘመን ከ1.2 ሚልዮን በላይ መፅሀፍትን አሳትሞ ለማሰራጨት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የትምህርት ዘመኑን ስኬታማ ለማድረግ ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ “የጋራ ርብርብ ለላቀ የትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ቃል የንቅናቄ ተግባራት በሰፊው በመካሄድ ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል።

በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻልና ለመማር ማስተማር ምቹ ለማድረግ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በህብረተሰብ ተሳትፎ ከ1 ቢልዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የመምህራን አቅም ማጎልበት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ያለውን የጎላ አስተዋጽኦ የገለፁ አቶ አልማው በዚህም በክልሉ ከ2613 በላይ መምህራንና የትምህርት አመራሮች የክረምት የአቅም ግንባታ ስልጠና እየወሰዱ ይገኛሉ ብለዋል።

ህብረተሰቡ ለትምህርት ጥራት የጀመረውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍና ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በክልሉ የተማሪዎች ውጤት ካለፉት አመታት እየተሻሻለ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን በዘርፉ የሚፈለገውን ስኬት ለማግኘት ብዙ የሚሰሩ ተግባራት እንዳሉም ቢሮው አሳውቋል።

የሴቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሳትፎ እንዲሁም የማለፍ ምጣኔ እየተሻሻለ መምጣቱም ተገልጿል።

በክልሉ የ2018 ትምህርት ምዝገባ የሚጀመረው ከነሀሴ 19/2017 ጀምሮ እንደሆነም ሀላፊው አብራርተዋል ስል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *