
በሀገራችን የትምህርት ጥራት ላይ እያጋጠሙ ያሉ ስብራቶችን ለመጠገን በመንግስት በኩል በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልም ይህንን የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመፍታት በክልሉ በትምህርት ቢሮ በኩል የጀመሩት በርካታ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የገለፁት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የመማር ማስተመር ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ደስታ ገነሜ ለዚህም በክልሉ አጠቃላይ በትምህርት ስርዓቱ ላይ ያለውን ጉድለት ከማሟላት አንፃር በልዩ ሁኔታ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ የተማሪዎች የመማር ውጤታማነትን ማሻሻል ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑና ለዚህም የትምህርት ቤቶች አካባቢን ለተማሪዎች ምቹ ለማድረግ በህብረተሰብ ተሳትፎ የመማሪያ ክፍሎችን መጠገን፣ አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች የመገንባት እና አጠቃላይ የትምህርት ቤቶች ለትምህርት ሥራ ምቹና ማራኪ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
በክልሉ በባለፈው ዓመት የተጀመረው “ትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄን በየዓመቱ በማስካሄድ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል እየተሰራ ነው ያሉት ዶ/ር ደስታ በክልሉ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ80% በላይ የሚሆኑ ለተማሪዎች ምቹ አለመሆናቸውንና ከሚፈለገው ደረጃ በታች መሆናቸው ዝቅተኛ የተማሪዎች ውጤት እንዲመዘገብ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን ለማሻሻል እንደክልል ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ስብራት የረዥም ጊዜ ችግር በመሆኑ የተጀመረውን ሁሉ አቀፍ ንቅናቄ በማጠናከርና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በማሳደግ ስብራቱን ለመጠገን ትኩረት የተሰጠ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ለዚህም ሰፊውን ድርሻ ማህበረሰቡና የአከባቢው ባለሀብቶች ወስደው እየተረባረቡ ያሉ መሆናቸውን አንስተው ይህም በ2017 ዓ.ም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የክልሉን የመማር መስተማር ስራ ውጤታማ ለማድረግ ከታችኛው ቅድመ አንደኛ ደረጃ ጀምሮ ትኩረት እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ደስታ የትምህርት ቤት አመራሩንና መምህሩን አቅም ማጎልበት አስፈላጊ በመሆኑ እየተሰራበት እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ከትምህርት ማህበረሰብ ጋር በመወያየት እና ዕቅድ በማውረድና በመገምገም በጋራ እየተሰራ መሆኑን ያብራሩት ኃላፊው የመምህራንን አቅም ለማጎልበት ስድስት ሺህ የሚሆኑ አንደኛ ደረጃ መምህራንን በፈተና በመመዘን የመለየት ስራ መከናወኑን የጠቀሱት ኃላፊው በቀጣይም የአቅም ውስንነቶችን በመፈተሽ አቅማቸውን የማጎልበት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ላይም ከአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ጋር ተያይዞ የመምህራንን አቅም ማጎልበት በማስፈለጉ ከትምህርት ሚንስቴር ጋር እየተሰራ ያለ ስራ መኖሩን የገለፁት ዶ/ር ደስታ በዚህም በዩኒቨርሲቲዎች ገብተው አቅማቸውን እንዲያሰድጉ በዚህ ክረምት የተጀመረ መሆኑን ጠቅሶ ይህንን በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልፀዋል፡፡
በክልሉ የትምህርት ግብዓት ለማቅረብ ባለፈው ዓመት ለ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ቅድሚያ በመስጠት ከክልሉ መንግሥት በተበጀተው 50 ሚሊዮን ብር መጽሐፍ በማሳተምና ከትምህርት ሚንስቴር ድጋፍ የተደረገውን 1.8 ሚሊዮን መጽሐፍትን ለተማሪዎች ማቅረብ መቻሉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ከመመሪያ መጽሐፍ አቅርቦት አንፃር አርብቶ አደርና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች በሚል ተለይቶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በሁሉም ዞኖች በአከባቢ ቋንቋ የሚሰጡ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍሎች የአከባቢውን ህብረተሰብና ባለሀብቶችን በማስተባበር ሀብት በማሰባሰብና ከየዞኖቹ ተጨማሪ ሀብት በመመደብ የተማሪዎችን የመማሪያ መጽሐፍት በማሳተም አገልግሎት ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ነው ያሉት ኃላፊው በትምህርቱ ሴክተር ድጋፍ የሚሹ አካላትን በተቀናጀ ሁኔታ ማገዝ አስፈላጊ በመሆኑ በክረምት በጎፍቃድ አገልግሎት የደም ልገሣ እና የድሃ ድሃ ቤት በመገንባት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት ወደ 25 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናግሩት ዶ/ር ደስታ በዚህም የተለያዩ ረጂ ተቋማትን በማስተባበር፣ ህብረተሰቡን በማሳተፍ፣ የወጣቶች እና የበጎፈቃደኞች አደረጃጀትን በማጠናከር፣ ሀብት በማሰባሰብ ለ 3 ሺህ ተማሪዎች የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ እንድደረግላቸው መደረጉን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ምዝገባና ሌሎች ዝግጅቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውንም ያወሱት ኃላፊው በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ልጆቻቸውን ያላስመዘገቡ ወላጆች ፈጥነው እንዲያስመዘግቡ እና የተመዘገቡትንም ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ለትምህርት ስራ የታቀደው ዕቅድ የሁሉም ድጋፍ የሚፈልግ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ደስታ እንደ ክልል የትምህርት ስብራትን በመጠገን በዘርፉ ውጤት ለማስመዝገብ የተጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ለማስቀጠል የትምህርቱን ሥራ ከመከታተልና ከማገዝ አኳያ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
