#ሪፖርታዥ

Spread the love

የመማር ማስተማር ሥራን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ  ትምህርታዊ ኢንሼቲቮች ተቀርጸው ተግባራዊ እየሆኑ ነዉ ፦የክልሉ ትምህርት ቢሮ

በክልሉ የመማር ማስተማር ሥራን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ የተለያዩ ትምህርታዊ ኢንሼቲቮች ተቀርጸዉ እየተተገበሩ እንደሚገኙ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

የመማር ማስተማር ሥራን ውጤታማ ለማድረግ ተቀርጸዉ እየተተገበሩ ከሚገኙ ሂደታዊ ከሆኑ ከተለያዩ ኢንሼቲቮች ወይም ትምህርታዊ ፕሮግራሞች አንዱ የትምህርት ቤት አምባሳደር ነዉ።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊና የመማር ማስተማር እና ምዘና ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር ደስታ ገነመ  እንዳሉት በክልሉ ከሚገኙ 184 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ165 ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት አምባሳደር ተሰይመው ወደ ስራ ገብተዋል።

በትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት አምባሳደር መሰየሙ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ፣ ተማሪዎች ውጤት እና ሥነ-ምግባር መሻሻል ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ነዉ ዶክተር ደስታ የገለጹት።

የትምህርት ቤት አምባሳደር የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ከማሻሻል አንጻር ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ምቹ እንዲሆኑ ያግዛል ያሉት ኃላፊው እንደሀገር የተጀመረውን የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በማጠናከር ማህበረሰቡ በባለቤትነት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የድርሻውን እንዲወጣ ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

እስካሁን በክልሉ ካሉት ከ184 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ165 ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቤት አምባሳደር ተሰይመው እንቅስቃሴ መጀመሩንና በዚህም የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግባራትን በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ነዉ ዶክተር ደስታ ገነመ የጠቆሙት።

አምባሳደሮቹ ከሚተገብራቸው  አንዱ ትምህርት ቤቶች የውስጥ ገቢ እንዲያድግ  እና ትምህርት ቤቶች ሀብት እንዲያፈሩ ብርቱ ድጋፍና ክትትል ሥራዎችን ዘርግተው ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ለአብነትም የትምህርት አምባሳደሮች በተመደቡባቸው ትምህርት ቤቶች ተጀመርው የቆሙ መማሪያ ክፍሎች ግንባታ ቀጥለዋል፤ ከማህበረሰቡ የተለዩ ትምህርት ቤቶች ከማህበረሰቡ ተቀራርበው የተማሪዎችን ውጤት እና ስለትምህርቱ ደረጃ ማሻሻያ ስልቶች ላይ ውይይት ጀምረዋል ብለዋል።

ከዚሁም ባለፈ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የተመደቡ አምባሳደሮች የትምህርት ቤቶቻቸውን መምህራን አቅም በማጎልበት በተመደቡበት ትምህርት ቤት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እየሰሩ እንደሆነ ዶ/ር ደስታ ገነሜ አብራርተዋል።

በክልል ደረጃ የትምህርት ቤት አምባሳደሮች ተሰይመው ወደ ተግባር ከገቡ ወዲህ  የትምህርት ልማት ሥራን ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል ብሎም የትምህርትን ስብራት መጠገን የሚያስችል ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኝም በመጥቀስ ሥራውን በየጊዜው በመገምገም ውጤታማነቱን ማረጋገጥ ክፍተቶችን የማረም ሥራ ይሰራል ብለዋል።

በትምህርት ቤቶች ተሰይመው በተለያዩ ምክንያት ወደ ተግባር ያልገቡ አምባሳደሮች በፍጥነት ወደ ሥራ በመግባት ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዉ አምባሳደር ባልተመደበባቸው ትምህርት ቤቶች አምባሳደር እንዲሰየሙ በማድረግ የተማሪዎችን ውጤት እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በማከልም ዶክተር ደስታ ገነመ፤ የትምህርት ልማት ሥራ ላይ በትኩረት መስራት በሁሉም ልማት ላይ ውጤታማ ለመሆን የሚረዳ በመሆኑ የትምህርት ቤት አምባሳደር ፣ የተማሪ ወላጆች፣ ማህበረሰብ እና ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ለትምህርት ልማት ሥራ ውጤታማነት ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ ድርሻቸውንም እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *