በአካባቢያችን እየተገነባ በሚገኘው የመስኖ አውታር የስራ ዕድል ተፈጥሮልናል፤ የተሻለ ልምድም እያገኘንበት ነው አሉ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች።

Spread the love

በ68 ሚሊዮን ብር ካፒታል በጀት እየተገነባ የሚገኘው የውኒ አነስተኛ መስኖ ግንባታ ፊሲካል ስራው 70 ከመቶ በላይ መድረሱ ተገለጸ ፡፡

የመስኖ ግንባታው በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት እንዲገባ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል እየተገነቡ ከሚገኙ የመስኖ ተቋማት አንዱ የሆነው የውኒ አነስተኛ መስኖ ግንባታ 68 ሚሊዮን ብር በሆነ ካፒታል በጀት እየተገነባ እንደሚገኝ በክልሉ የመስኖ ተቋማት ልማትና አስተዳደር አገልግሎት ኤጀንሲ በዳውሮ እና ኮንታ ዞኖች የፕሮጀክቶች መሃንዲስ የሆኑት አቶ ቻላቸው ሽንቁጤ ተናግረዋል ፡፡

በክልሉ ዳውሮ ዞን ማረቃ ወረዳ በጌንዶ ባቾ ቀበሌ እየተገነባ የሚገኘው የውኒ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ተሰርቶ ሲጠናቀቅ 140 ሄክታር መሬት ማልማት እንዲችል ተደርጎ እየተሰራ እንዳለ ባለሙያው አብራርተዋል ፡፡

የውኒ አነስተኛ መስኖ ልማት 150 አባወራዎችን በተለያዩ የልማት ስራዎች ተጠቃሚ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ታልሞ እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ቻላቸው ሽንቁጤ አብራርተዋል ፡፡

የክልሉ የመስኖ ተቋማትና ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የፕሮጀክቶች አፈጻጸም በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት በብቁ እንዲሆኑ የክትትልና ድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው እየተሰሩ እንደሚገንም አቶ ቻላቸው አብራርተዋል ፡፡

ገዛኸኝ ዋጀቦ ህንጻ እና ውሃ ስራዎች ተቋራጭ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቱን ተረክቦ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት የፕሮጀክቱ ማናጀር አቶ ታደሰ ጃንቦ አሁን ላይ የፊሲካል ስራው 70 ከመቶ በላይ መድረሱን አብራርተዋል ፡፡

እስካሁን ባለው አፈጻጸም 2.4 ኪሎሜትር ዋና ቦይ ግንባታ ፣ ሁለተኛ ቦይ ቁፋሮ ስራ እንዲሁም የአናት ግንባታ ስራ መጠናቀቁንና ሌሎች ቀሪ ስራዎችን በሁለት ወራቶች ውስጥ ሰርቶ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኝም አብራርተዋል ፡፡

አሁን ባለው የግንባታ አፈጻጸም 80 ሄክታር መሬት ማልማት እንደሚቻልም አቶ ታደሰ ጃንቦ አብራርተዋዋል ፡፡

በውኒ አነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክት ከ150 ያላነሱ አካባቢው ወጣቶች ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውንም አቶ ታደሰ ጃንቦ ተናግረዋል ፡፡

ስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች በበኩላቸውም በሚያከናውኗቸው ስራዎች የተሸለ ልምድ እንዳገኙና በሚያገኙትም ሀብት ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መርዳት እንደቻሉም ተናግረዋል ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *