




መድረኩን በንግግር የከፈቱት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ጤናማ ዜጋን ለመፍጠር ኢንስቲትዩቱ በክልሉ የጤና ስጋት የሆኑ በሽታዎችን የመለየት፣ ቅድመ ዝግጅት የማድረግ፣ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመስጠትና የመከላከል ስራ እየሰራ ያለው አንጋፋ ተቋም መሆኑን አብራርተዋል።
የመረጃ ጥራት ለማሻሻልና ከዚህ በመነሳት አስፈላጊውን የግብዓት ችግርን ለማቅረብ፤ መረጃውን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመረጃ ጥራትን ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ለውጤታማነቱ በየደረጃው ያሉ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ጠይቀዋል።
የላቦራቶሪ ችግርን ለመቅረፍ ክልሉ ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በሚዛን አማን ቅርንጫፍ እና በቦንጋ ገ/ፃዲቅ ሸዋ ሆስፒታል ግንባታዎች የማካሄድናና ግብዓትን የማቅረብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።
በመሆኑም የበሽታ ቅኝት፣ ዝግጅትና ምላሽ ስራዎችን በተቀናጀ ሁኔታ ሞዴል ማድረግ፤ ለዚሁም ውጤታማነት ግብዓትን የማሟላት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተው ለውጤታማነቱ ጥራት ያለውን መረጃ ማቅረብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት በቢሮው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ወሰን ጨምሳ በኢንስቲትዩቱ በሸታን ቅኝት በማድረግ ምላሽ ከመስጠት ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በተሰራው ስራ 33 በመቶ መቀነስ መቻሉን ገልጸው አሁንም ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ተናግረዋል።
የመድረኩ ዓላማው በተቋሙ እስካሁን የተሰሩ ስራዎችን ማስተዋወቅና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ መወያየት እንደሆነ ያነሱት አቶ ወሰን በመረጃ ማዘመንና ጥራት ላይም ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት የስድስት ወር ሪፖርት በዳይረክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋጽዮን ተረፈ ለተሳታፊዎች እየቀረበ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ የጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊዎችን ጨምሮ የቢሮው የማኔጅመንት አባላት፣ የዞን መምሪያ ኃላፊዎች፣ የሆስፒታል ስራ አስኪያጆች፣ የወረዳ ባለሙያዎችና ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በጌታሁን ግርማ
