
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ160 በላይ ትላልቅ የግብርና ኢንቨስትመንት አልሚዎች መሰማራታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት የተገነቡት የቱሪስት መዳረሻዎችም የአካባቢው የሆቴልና ቱሪዝም አገልግሎት ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ በር መክፈታቸውን ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ በሁለት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑ የሰላምና ልማት ስራዎችን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለኢንቨስትመንት ምቹ አካባቢ፣ ሰፊ አምራች ሃይል፣ እምቅ የጥሬ እቃ አቅም ያለው ስለመሆኑ አንስተዋል።
ክልሉም ከምስረታ ጀምሮ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለመሳብ ልዩ የኢንቨስትመንት ፓኬጅ ቀርጾ ሲያስተዋውቅ መቆየቱን አውስተዋል።
በዚህም በተለይ በግብርናው ዘርፍ ክልሉ ያለውን ጸጋ አልምቶ ለመጠቀም ከ160 በላይ ትላልቅ የግብርና ኢንቨስትመንት አልሚዎች ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
በግብርናው መስክ ከተሰማሩ ኢንቨስተሮች መካከል ምርት ማቅረብ የጀመሩና ስራ ለመጀመር ዝግጅት እያጠናቀቁ የሚገኙ መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በተለይ ልዩ ጣዕም ያለው ቡናን ለማምረት እና እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ ለመላክ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍላጎት መኖሩን ነው ያነሱት።
አቮካዶን ጨምሮ ፍራፍሬ ማቀነባበር፣ የቅመማ ቅመምና የሻይ ምርት ላይም በርካታ ባለሀብቶች በመሰማራት ላይ ናቸው ብለዋል።
በክልሉ የነበሩ የጸጥታ ስጋቶችን ሙሉ ለሙሉ በመቅረፍ የማዕድን ዘርፉን የማነቃቃት ስራ መሰራቱንም ርዕሰ መስተዳድሩ አክለዋል።
በዚህም በተለይ በወርቅና በድንጋይ ከሰል ማምረት ዘርፍ ባለሀብቶች እየተሰማሩ መሆኑን ጠቅሰው የብረት ማዕድን ፍለጋ ላይ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ስለመኖራቸው አንስተዋል።
በሌላ በኩል ክልሉ የበርካታ ተፈጥሯዊ የመስህብ ስፍራዎች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተገነቡ ሎጅና ሪዞርቶች ለክልሉ ቱሪዝም መጠናከር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ናቸው ብለዋል።
አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች በርካታ ጎብኝዎችን ከመሳብ ባለፈ የክልሉን የሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ በር መክፈታቸውን አንስተዋል።
አካባቢው በግብርናው ዘርፍ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምቹ ሁኔታዎች ያሉት እና እምቅ ሀብት ያለው በመሆኑ ባለሀብቶች በፈለጉት የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም መዋእለ ንዋያቸውን ፈሰስ ለሚያደርጉ ባለሀብቶች አስፈላጊው መንግስታዊ አገልግሎት በተቀላጠፈ ሁኔታ እንደሚሰጣቸውም አረጋግጠዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
