ጥንታዊው የማህበረሰብ አስተዳደር ስርዓትና “ማሽቃሮ” በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት እንዲመዘገብ ተጠየቀ

Spread the love

ለዘመናት ተጠብቆ ለዓለም የበቃውና በዩኔስኮ የተመዘገበው የካፋ ባዮስፌር ሪዘርቭ የህልውናው መሰረት፣ የካፊቾ ህዝብ ጥንታዊ የአስተዳደር ስርዓት የሆነው “ምክረቾ” መሆኑ ተገለጸ። በመሆኑም ይህ ድንቅ ባህላዊ ስርዓትና መገለጫው የሆነው የማሽቃሮ በዓል፣ ተገቢውን ዓለም አቀፍ እውቅና በማግኘት በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስነት ሊመዘገብ እንደሚገባው ባለሙያዎችና አመራሮች አሳሰቡ።

ይህ የተገለጸው የማሽቃሮ በዓልንና የካፋ ባዮስፌርን 15ኛ ዓመት ምሥረታን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ ነው።

ውይይቱን የመሩት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ማስረሻ በላቸው፣ “የማሽቃሮ ትሩፋት የሆነው የካፋ ባዮስፌር ባገኘው ዓለም አቀፍ እውቅና ልክ፣ ለዚህ ስኬት መሰረት የሆነው የማሽቃሮ በዓልም በዩኔስኮ ተመዝግቦ ለዓለም ሊተዋወቅ ይገባል” ብለዋል።

የክልሉ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ኢንጂነር አስራት ገ/ማርያም በበኩላቸው፣ “ማሽቃሮና የካፋ ህዝብ ባህላዊ የደን አጠባበቅ ዘዴ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው” ሲሉ የሁለቱን ጥብቅ ቁርኝት አስረድተዋል። “በቅርስነት የተመዘገበው ባዮስፌር ህልውናው እንዲቀጥል ከተፈለገ፣ ባለቤቱ የሆነው ህዝብ ማንነትና የጥበቃ ጥበብ የሆነው ‘ማሽቃሮ’ በቅርስነት መመዝገብ አለበት” በማለት ለዓለም አቀፍ ተቋማት የትብብር ጥሪ አቅርበዋል።

ማሽቃሮ በዓለም ደረጃ ጎልቶ እንዲታይ በሌሎች ተጨማሪ የነገስታት ቅርሶች ላይ ሰፊ ጥናት እየተደረጉ መሆኑን የጠቆሙት የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻው ከበደ ይኸንን ሂደት የሚያሳልጡ ባለድርሻዎች በተገኙበት የሚናከብረው በዓል መሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ አበራ ስዩምም፣ “የካፋ ማህበረሰብ የሚታወቅበት የደን ጥበቃ፣ የማሽቃሮን በዓል ተከትሎ በሚደረገው ‘የምክረቾ’ የግምገማ ስርዓት ውጤት መሆኑን ተገንዝበናል” ብለዋል። አክለውም፣ “ይህ ባዮስፌር የሀገሪቱን ከፍተኛ ድርሻ የሚሸፍን የብዝኃ ህይወት የያዘ በመሆኑ፣ ጥበቃው ሊጠናከር ይገባል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የውይይት መድረኩ የባህል ጥበቃው ከዘመናዊ የልማት ስራዎች ጋር መጣመር እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥቷል። በተለይም የነገሥታት መናገሻ የሆነችዉ ቦንጋ ከተማ፣ የባዮስፌሩ ማዕከል እንደመሆኗ መጠን ለቱሪዝም በሚመጥን መልኩ እንድትለማና “ቦንጊ ሻምበቶ” የተሰኘው ልዩ መንደር ከከተማው ጋር እንዲተሳሰር ሰፊ ስራ መሰራት እንዳለበት ተገልጿል።

ይህንን ታላቅ ራዕይ ለማሳካትም የብሔሩ ተወላጆች፣ ባለሀብቶችና የካፋ ወዳጆች በሙሉ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

በፓናል ውይይቱ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ አምባሳደሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸው ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል።

በአሻግሬ ገ/ወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *