










በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በከተሞች የመልካም አስተዳደርና የልማት ተግባራት ላይ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በቦንጋ እያካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጅነር የማታለም ቸኮል የመድረኩ ዓላማ ሀገራችን ለከተማ ልማት ከሰጠችው ትኩረት፣ ከከተሞች ተለዋዋጭ ባህሪና የህዝብ ቁጥር በየጊዜው ከመጨመር አንጻር ስራው ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ እስካሁን የመጡ ለውጦችን በመገምገም፣ ያጋጠሙ ማነቆዎችን በመለየት፣ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ መግባባት ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።
አክለውም በከተሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን በማንሳት ያልተከናወኑ ብዙ የቤት ስራዎችና ያልተፈቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖሩን በመጠቆም በትኩረት መፍታት እንደሚገባ አንስተዋል ።
በከተሞች በመሠረተ ልማት አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱን የገለጹት ኢንጂነር የማታለም የህዝብ ውይይት መድረክን በማጠናከር መተማመን በመፍጠር ልማትን ማፋጠንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በትኩረት መፍታት ለከተሞች ዕድገት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በከተሞች ሀብትን መፍጠር፣ የተጀመሩ የኮርደር ልማት ስራዎች ማጠናከር፣ የመሬት አቅርቦትና ምዝገባ ስርዓት ማሻሻል፣ የከተማ ውበትና ጽዳትን ባህል ከማድረግ፣ኢንቨስትመንት ከመሳብ፣ የገቢ አቅሞችን በመለየት አሟጦ ማሰባሰብና መሬት የተረከቡት ባለሀብቶች እንዲያለሙ ከማድረግ እንዲሁም ለስራ ምቹ አካባቢ ከመፍጠር አንጻር ተሳታፊዎች በጥልቀት በመወያየት በቀጣይ በትኩረት መስራት እንደሚሻ በአጽንኦት ተናግረዋል።
የስድስቱ ዞኖች ዋና ከተሞች የ6 ወራት አፈጻጸም በማዘጋጃ ቤታዊ ስራ አስኪያጆች ለተሳታፊዎች እየቀረበ ይገኛል ።
በምክክር መድረኩ ላይ የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የዞን መምሪያ ኃላፊዎች፣ የከተማ ካንቲባዎች፣ የማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጆች፣ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ ።
በጌታሁን ግርማ
