በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቤንች ሸኮ ዞን ተወካዮች ከዞኑ የካቢኔ አባላት ጋር በዞናዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እያካሄዱ ነው።

Spread the love

የፓርላማ አባላቱ በቀጣይም በዞኑ በትምህርት ፣ ጤና ፣ የመንገድ እና የውሀ ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው የሚጎበኙ ሲሆን ከወከሏቸው ህዝብ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍትን እንደተናገሩት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዞኑ ተወካዮች በተለያዩ ጊዜያት ወደ ህዝቡ እየወረዱ የተለያዩ የልማት ስራዎችን የመጎብኘትና ከወከሉት ህዝብ ጋር መድረኮችን እየፈጠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላቱ በተጨባጭ ከህዝቡ ጋር በሚያደርጉት ውይይትና በመስክ ምልከታ የሚያገኟቸውን ግብዓቶች ለአስፈጻሚ ተቋማት በማቅረብና በመነጋገር በሚፈቱበት መንገድ ላይ አቅጣጫ እየተቀመጠ ሲመራ መቆየቱን ገልጸዋል።

የሚዛን አማን ውሀ ስርጭት ፍትሀዊ አለመሆን እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ላይ ከተማው የሚያመነጨው ውሀ በቂ አይደለም ብለዋል። ለዚህም የሚዛን አማን የውሀ ማስፋፊያ ስራ ከክልሉ መንግስትና ከሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር መነጋገር ተችሏል ብለዋል።

የግዝመሬት ፣ ማዝና መሰል የጥልቅ ውሀ ግንባታዎች በቅርቡ ተመርቀው ስራ ይጀምራሉ ብለዋል። የሚዛን ቴፒ የአስፓልት ስራ በሚጠበቀው ፍጥነት ልክ ባይሆንም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚዛን አማን ዲማ የአስፓልት መንገድ ስራ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አመራሮች ጋር የውይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን የአስፓልት ስራው በአዲስ መልክ እንደሚሰራ መግባባት ላይ መደረሱን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።ከቂጤ ደብረ ወርቅ የጥገና ስራ በቅርቡ ይሰራል ብለዋል። በሰሜን ቤንች ፣ ጉራፈርዳ ፣ ሸኮ ፣ ሼይ ቤንች ወረዳም የተለያዩ ቀበሌዎች የጥገና ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር በኮሪደር ልማት ከህዝቡ ከ14 ሚሊየን ብር የተሰበሰበ ሲሆን 3 ኮንትራክተሮችን ወደ ስራ በማስገባት ከ980 ሜትር በላይ የዲች ቦይ ፣ የቴራዞን ንጣፍና መሰል የግንባታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተገልጿል።በትምህርት አምና በሁሉም መዋቅር ከ129ሺ በላይ ተማሪዎች በመደበኛ ትምህርት የተመዘገቡ ሲሆን ዘንድሮ ከአምናው በ8ሺ ተማሪ ብልጫ ያለው መሆኑም ተገልጿል።የዞኑ መንግስት ከ46 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከ1-6ኛ ክፍል በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጻህፍት ህትመት ተከናውኗል።

በጤናው ዘርፍ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን በንቅናቄ እየተሰራ ነው ። የመድሀኒትና የግብዓት አቅርቦት ችግሮች ስራው ላይ ተግዳሮት መፍጠሩ ተጠቁሟል። ከህዳር ወዲህ የወባ በሽታ ጫና የቀነሰ ቢሆንም አሁንም የመድሀኒት እጥረት ይታያል ተብሏል። በጊዲ ቤንች ተጨማሪ ጤና ጣቢያ በዞኑ መንግስት ለመገንባት የጨረታ ሂደት ላይ መሆኑ ተገልጿል።

በትራንስፖርት ዘርፍ ዲጂታል የመነሀሪያ አገልግሎትን በማቋረጥ የኢ-ቲኬቲንግ ስራ በመነሀሪያው እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል። የህዝብ ፍሰትና በመነሀሪያው የሚገኙ ተሽከርካሪዎች እጥረትና የመነሀሪያ ግቢ እጥረት ፣ የአዲሱ መነሀሪያ ግንባታ አለመጠናቀቅ አሁንም ችግር ሆነው መቀጠላቸው ተገልጿል። በተለይም ከ2013 ወዲህ በአብዛኛው በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች በገጠር ተደራሽ መንገድ ግንባታ የተጀመሩ ስራዎች አለመጠናቀቅ ዛሬም የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው መቀጠላቸው በመድረኩ ተነስቷል።

በስራ ፣ ክህሎት ፣ ኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ከ7ሺ 604 በላይ ስራ አጥ ወጣቶች ስልጠና መሰጠቱም ተገልጿል። በወቅት ስራ ስምሪት ከ30ሺ በላይ ስራ አጦች የስራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን በቋሚ ስራ ዕድል ለ2ሺ 327 ወጣቶች ስራ መፈጠሩ ተገልጿል። ዕዳ ከማስመለስ አንጻር 22 ሚሊየን 364ሺ 751 ብር ማስመለስ መቻሉ በመልካም ጎኑ ተነስቷል ሲል የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *