




“ጠንካራ የወጣቶች ክንፍ ለጠንካራ ፓርቲ መሠረት ነው”በሚል መሪ ቃል በ2ኛ የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ዙሪያ የብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ሚና በሚል የውይይት መድረክ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ተካሂዷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰይድ ኢብራሂም በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆኑ ገንቢ የሆኑ ሀሳቦችን በማፍለቅ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት አሻራቸውን ማኖር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ፣በሰላም ግንባታ ፣በልማት ስራዎች ወጣቶች ግንባር ቀደም በመሆን የፓርቲውን ተልዕኮ በጋራ መፈፀም ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ሸካ ዞን ቅ/ጽ/ቤት የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊና ረዳት የመንግሥት ተጠሪ አቶ ዘርሁን አንደሞ በበኩላቸው በ2ኛ የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች መሠረት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ልያረጋግጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ፓርቲው በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመሆኑም ወጣቶች በፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎች በመሳተፍ በመንግሥት የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳዳር ስራዎችን በመደገፍ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ገልፀዋል።
የቴፒ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊና ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ ዋሲሁን አውሎ በወቅቱ እንደተናገሩት እንደ ሀገር ብዙ ቁጥር የያዙት ወጣቶች ከመሆናቸው አንፃር ባላቸው እውቀት ሀገርን በሁሉም ዘርፍ ማገልገል ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የከተማውን አልፎም የዞኑን ልማት ለማፍጠንና ሰላምን ለማፅናት ወጣቶች እያደረጉ ያሉት ተሳትፎ የሚመሰገን እንደሆነ ገልፀው ይህም ተጠናክሮ ልቀጥል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ሸካ ዞን ወጣቶች ክንፍ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ወጣት ሳይሉሽ ግዛው በ2ኛ የብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ዙሪያ የወጣቶች ሚና የሚል የመወያያ ሰነድ ባቀረቡበት ወቅት ወጣቶች ገዥ ትርክትን በማፅናት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
በቀረበው ሰነድ መነሻ በመድረኩ የተሳተፉ ወጣቶች በበኩላቸው ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ የወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው ለኑሮ ውድነት ምክንያት የሆኑ ነገሮችን በመፈተሽ መፍትሔ ማበጀት ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
በመድረኩ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ ወጣት ሰይድ ኢብራሂም፣በብልፅግና ፓርቲ ሸካ ዞን ቅ/ጽ/ቤት የፖለቲካና ህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊና ረዳት የመንግሥት ተጠሪ አቶ ዘርሁን አንደሞን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ ወጣቶች ክንፍ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የወጣት ክንፍ አመራሮች እንዲሁም የከተማ ወጣቶች ተሳትፈዋል ሲል የዞኑ መንግስት ኮሚኒኬሽን ዘግቧል።
