

ምሁራኑም የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫና ምስጋና በዓል ቢስት ባር ለሀገራችን ቱሪዝም ዕድገት የጎላ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል፡፡
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የ2024 የማንዴላ ዋሽግተን ፎሎዉ አሸናፊ ረዳት ፕሮፌሰር ታገል ወንድሙ እንዳስረዱት የቤንች ሕዝብ የራሱ የሆነ ማንነት ፣ ለየት ያለ የዳኝነት ሥነ-ሥርዓት ፣ የአመጋገብና የአለባበስ ሥርዓት ያለዉ ሁሉን አቃፊ ሕዝብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ብሔረሰቡ በዱም ሥርዓት የሚተዳደር ነዉ የሚሉት ረዳት ፕሮፈሰሩ ቴርቶሪያል ዴሞክራሲን የሚከተል እና ሀገር በቀል የቀን አቆጣጠር የሚከተል እንዲሁም የራሱ የሆነ የለቅሶ ሥርዓት የሚከተል ሕዝብ ነዉ ብለዋል፡፡
አክለዉም ብሔረሰቡ ወደ 13 የሚጠጉ በዓላት ሲኖሩት ከዚህ ዉስጥ አንዱ የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫና ምስጋና በዓል ቢስት ባር ነዉ ብለዉ ምርቱ ቀድሞ የደረሰለት ሰዉ ሌሎችን የሚያቃምስበት ወይም የቅምሻ በዓል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቢስት ባር ለቱሪዝም ከፍተኛ ዕድል እየከፈተ ባህላችንን ወደ መሸጥ ደረጃ ደርሰናል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ታገል ካሁኑ እንኳን በቲ-ሸርት ፣ ኮፊያ ፣አልባሳት በመስራትና ባህላዊ ምግቦችንና መጠጦች በማዘጋጀት እንዲሁም በኪነ ጥበቡ ዘርፍ ከፍተኛ ገቢ የማመንጨት ስራዎች እየተሰሩ ነዉ ብለዋል፡፡
በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ መምህር ፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግስት ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወጣት ይስሃቅ ንጉሴ በበኩላቸዉ ቢስት ባር የክረምት ጭጋግ አልፎ ብርሃን የሚበራበት ፣ እህሉ ፍሬ አፍርቶ ሰዎች የሚቃመሱበትና ለመጣዉ ዉጤት ፈጣሪያቸዉን የሚያመሰግኑበት በዓል ነዉ ብለዋል፡፡
አክለዉም ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ማዕከል አድርጋ ከምትሰራቸዉ ሰስራዎች ዋነኛዉ የቱሪዝም ዘርፍ ሲሆን ቢስት ባር ለዚህ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንዳለዉ አስረድተዋል፡፡
የቤንች ብሔር የዘመን መለወጫና ምስጋና በዓል ቢስት ባር የሀገር በቀል ዕዉቀት እንደመሆኑ የምሁራን ጥናት ታክሎበትና ዕሴቶች ተጨምረዉበት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ባህላችንን ለመሸጥ ምሁራኑ ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል፡፡
ሕዝቡ ለቢስት ባር በዓል አካባበር የሚያደርገዉ ንቅናቄና ተነሳሽነቱ አስደሳች ከመሆኑ ባሻገር የቤንች ብሔር ባህል ሳይበረዝ ተጠብቆ እንዲቆይ የወጣቶች ሚና ወሳኝ መሆኑን አክለዋል ምሁራኑ፡፡
ምሁራኑ ለመላዉ የቤንች ሕዝብ ፣ የቤንች ሸኮ ሰዞን ሕዝቦች ፣ የአጎራባች ዞኖች ነዋሪዎች እና ለመላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለ2017 ዓ/ም የቢስት ባር በዓል አደረሳችሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸዉን መግለጻቸዉን የቤንች ሸኮ ዞን ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
በስተመጨረሻም ኑ የበኩር እህላችንን አብረን ቀምሰን በድምቀትና በአብሮነት ቢስት ባርን እናክብር ሲሉ ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል፡፡
