




ጊፋታ፣ የወላይታ ህዝብ የአዲስ ዓመት ፌስቲልቫል፣ በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ተመዝግቧል።
ቅርሱ የተመዘገበው እአአ ከታህሳስ 8 እስከ 13፣ 2025 በህንድ፣ ኒው ዴይሊ እየተካሄደ በሚገኘው 20ኛው የዩኔስኮ የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ጥበቃ የመንግሥታት ኮሚቴ ጉባዔ ላይ ነው።
ኢትዮጵያ በጉባዔው በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት እንዲመዘገብ ያቀረበችው ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ጊፋታ የወላይታ ህዝብ የአዲስ ዓመት ፌስቲቫል ሲሆን፤ ዛሬ ዩኔስኮ መዝገቡን ተቀብሎ ቅርሱን በሰው ልጆች ወካይ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስነት መዝግቧል።
ጊፋታ፣ ዩኔስኮ ቅርስን በሰው ልጆች ወካይ ኢንታንጀብል ቅርስነት ለመመዝገብ ያስቀመጣቸውን አምስት መመዘኛዎች አሟልቶ በመገኘቱ በማህደሩ ለመመዝገብ ችሏል።
ጊፋታን በሰው ልጆች ቅርስነት እንዲመዘግብ ካበቁት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል በዓሉ እድሜ፣ ፆታ፣ ሃይማኖት እና ማህበራዊ ደረጃን ሳይለይ የሚያሳትፍ መሆኑ፣ የቅርሱ ተስተላልፎም ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑ፤ በትምህርት ቤቶችና በሚዲያዎች ለትውልድ በመሸጋገር ላይ የሚገኝ መሆኑ፤ በዓሉ ሰላምን፣ አንድነትን እና አብሮነትን የሚያበረታታ መሆኑ የሚሉት ይገኙበታል።
ለዘላቂ ልማት፣ የምግብ ዋስትናን ከፍ በማድረግና አካባቢን ከመጠበቅ አንፃር ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑ፤ ኖሚኔሽን ፋይሉ በቅርሱ ባለቤቶች ነፃና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ተሳትፎ የተከናወነ መሆኑ እና ቅርሱ በሀገሪቱ ብሔራዊ ምዝገባ ውስጥ የተካተተ መሆኑም ቅርሱ ለመመዝገቡ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በቪድዮ ኮንፍረንስ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ጊፋታ የፆታ፣ የዕድሜ፣ የሃይማኖትና የማኅበራዊ አስተዳደግ ልዩነት ሳይደረግ ሰዎችን ያሰባስባል ብለዋል።
ከበዓሉ በፊት ባሉት ቀናት ማኅበረሰቦች አካባቢያቸውን በማጽዳትና በማስዋብ፣ ቤቶችን በማደስ፣ ዛፎችን በመትከል እና ተጋላጭ ለሆኑ ቤተሰቦች ድጋፍ በመስጠት ሕይወት ይዘራሉ፤ ወዳጅ ዘመዶች ይገናኛሉ፤ እና የቆዩ አለመግባባቶችም በሰላም ይፈታሉ ብለዋል ወ/ሮ ሰላማዊት።
ይህም ማኅበረሰቦች ግንኙነታቸውን አጠናክረውና መንፈሳቸውን አድሰው ወደ አዲሱ ዓመት እንዲገቡ ያስችላቸዋል ብለዋል።
በዩኔስኮ የተሰጠን ዕውቅና ለዎላይታ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ጥልቅ ትርጉም አለው፤ ቅርሱን ለመጠበቅ ያለንን ቁርጠኝነትም ይበልጥ ያጠናክረዋል ማለታቸዉን ኢቢሲ ዘግቧል።
