
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለ3ኛ ጊዜ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔረሰቦች ቀን በዓል በድምቀት እንዲከበር ሰፊ ስራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።
ለበዓሉ ድምቀት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የገለፁ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ በዓሉ በክልሉ ሁሉም አከባቢዎች ከቀበሌ ጀምሮ በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ ቦታዎች በድምቀት እየተከበረ መቆየቱን አስረድተዋል።
የተከበሩ አቶ ወንድሙ አክለውም የብሔረሰቦች ቀን በዓል በክልሉ ያሉ 13 ብሔረሰቦች የየራሳቸውን ቱባ ባህል ለሌላው የሚያስተዋውቁበት ትልቅ መድረክ እንደሆነም አንስተዋል።
የበዓሉ አከባበር ይዘት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደመጣ ያስረድቱ አፌ ጉባኤው በዓሉ የብሔሮችን የእርስበርስ ግኑኝነት እንደሚያጠናክረም አስረድተዋል።
በዘንድሮ የብሔረሰቦች ቀን በዓል የክልሉን ቱባ ባህልና የተለያዩ ወጎችን ከወትሮ በተለየ መልኩ ለማስተዋወቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ተብራርቷል።
ለበዓሉ ዝግጅት ከክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑም የተገለፀ ሲሆን በየደረጃው የተቋቋመው ኮሚቴዎች በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛሉም ተብሏል።
በዓሉ ለክልሉ ገፅታ ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ኤንደሆነ የገለፁ አፌ ጉባኤው በህዳር 29/2017 በአርባምንጭ ከተማ በሚካሄደው አገር አቀፍ መድረክ በተደራጀ ሁኔታ ተሳትፎ ይደረጋልም ብለዋል።
ለበዓሉ ስኬታማነት በየደረጃው ያለው የባለድርሻ አካላት ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ተላልፏል።
