
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ለሀገሪቱ ፖልሲ ቀረፃ ግብዓት ከመሆኑም ባሻገር የዜጎችን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ጉልህ ድርሻ አለው
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በሀገር ደረጃ በአዋጅ 760/2004 ፤ በተሻሻለው 1049/2009 ተደንግገው ለሰብዓዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ መብቶች እንድሁም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃምነትን በቋሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል ህጋዊ መረጃ ለዜጎችና ለመንግስት ለማቅረብ የሚሰራ ዘርፍ ነው፡፡
የሲቪል መረጃ ምዝገባ ከየትኛውም መረጃ በላይ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ከፌደራል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ከነዝህ ምዝገባዎች የተገኙ መረጃዎች ለግለሰቦች፣ተቋማት፣ድርጅቶችና መንግስት ግብዓት ሆኖ እያገለገሉ ነው፡፡
እንደ ክልላችን ዘርፉ በሚፈልገው ኩነቶች (በልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ፣ ፍቺና ጉድፈቻ) ላይ የተለያዩ መንግስት ተቋማትን ባደራጀ መልኩ ታቅዶ እየተሰራ እና የተሻለ አፈጻጸም እየተመዘገበ መሆኑን የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
በክልላችን በሚገኙ ቀበሌያት የወሳኝ ኩነቶችን ምዝገባ ማካሄድ እንዲቻል ዘንድ ክልላችን ከተደራጀበት ጊዜ አንስቶ ለቀበሌያት “የምዝገባ ኮድ” በመስጠት ወደ ምዝገባ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ተሰርው ተግባሩ በተሻለ ሁኔታ እየተመራ ይገኛል፡፡
በዚሁ መሰረት እስካሁን በመደበኛ የምዝገባ ተግባር ውስጥ የሚገኙ ቀበሌያት ብዛት በየአመቱ 5% እየጨመረ አሁን ላይ የምዝገባ ሽፋን በበጀት ዓመቱ በክልሉ በሚገኙ በ930 ቀበሌዎች የምዝገባ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ም/ኃላፊና የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ደነቀ ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ከተለያዩ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ አፈፃፀሙ በየዓመቱ 20% የምዝገባውን ዕቅድ በማሳደግ በበጀት ዓመቱ በ5ቱም ኩነቶች 73 ሺ 87 ለመመዝገብ ታቅዶ 72 ሺ 374 (99 %) መመዝገብ መቻሉን ገልፀው ይህ አፈፃፀም የክልላችን መንግስት የሚመለከታቸውን ተቋማት በማስተሳሰር ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል በማድረጉ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ከ 5ቱ ኩነቶች የልደት ምዝገባ 50 ሺ ለመመዝገብ ታቅዶ 56 ሺ 239 (112%) ፣ ፍቺ 1 ሺ 881 ለመመዝገብ ታቅዶ 2 ሺ 415(128%) እንድሁም ጋብቻ 13 ሺ ለመመዝገብ ታቅዶ 10 ሺ 781(83%) ማከናወን መቻሉን የገለፁት አቶ ሰለሞን በአንፃሩ የሞት(36%) እና ጉድፈቻ(12.6% ) ምዝገባ ዝቅተኛ አፈፃፀም መታየቱ የፈጠረውን የአሠራር ክፍተቶች ለማረም አቅጣጫ እንደተያዘ አውስተዋል፡፡
እነዚህ ምዝገባዎች ከቁልፍ ባለድርሻ አካላት (ተቋማት) ጋር በመቀናጀት የሚተገበሩ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን በጤና ተቋማት ውስጥ የተከሰቱ ልደትና ሞት ኩነቶች እዛው እንዲመዘገቡ መዝጋቢ ባለሙያ እና የሚያስፈልገውን ሎጀስቲክ በማሟላት በክልላችን ከምገኙ ጤና ተቋማት ውስጥ በ56 ተቋማት ውስጥ መተግባር ተችሏል ብሏል፡፡
ዋና ዋና ኩነቶችን በገጠር ቀበሌያት ደረጃ የመመዝገቡን ዓይነተኛ ሚና የሚወጡትን የክብር መዝገብ ሹሞችን እንዲሁም የቀበሌ ስራ አስከያጆችን ከክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ጋር ቅንጅታዊ አሰራር በመፍጠር የክልሉን ዕቅድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ኢንዲሻሻል እየተሰራ ይገኛል ያሉት አቶ ሰለሞን በፍርድ ቤቶች የሚወሰኑ ፍችዎችን ከጠቅላይ ፍ/ቤት ጀምሮ በየደረጃው ከሚገኙ ፍ/ቤቶች ጋር የጋራ መግባቢያ ሠነድ በመፈራረም ውሰኔ ያገኙ ፍችዎች እንዲመዘገቡ ዳኞች ትዕዛዝ የማስተላለፍ እና ለፍቺ ውጤት (ንብረት ክፍፍል) ሂደት የፍች ሰርተፍኬት እንደ ቅድመ-ሁኔታ መታየት መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
ከክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና ተያያዥ መዋቅሮች ጋር ቅንጅት በመፍጠር የሴቶችን አደረጃጀት በመጠቀም የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እና የተከሰቱ ኩነቶችን እንዲያስመዘግቡ በመደረጉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ማስረጃ ከሚሰጠው ጤቀሜታ አኳያ ህብረተሰቡ ተረድቶ የማስመዝገብ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑንም ኃላፊው አውስተዋል፡፡
ከትምህርት ቢሮ ጋር በተፈጠረው ቅንጅት የቅድመ-መደበኛ ተማሪዎች፣ የ6ኛ፣ የ8ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በዕድሜ መለያት ምክንያት የሚፈጠረውን የመረጃ መጣረስ ለመከላከል ተማሪዎች የልደት ሰርተፊኬት ይዘው በት/ቤቶች እንዲመዘገቡ እየተደረገም ነው ያሉትአቶ ሰለሞን የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን ወደ ድጅታል ለማስገባት በ2017 በጀት ዓመት ለ 703 ቀበሌያት ሲም ካርድና ፓኬጅ ከኢትዮ.ቴሌ.ኮም ግዥ በመፈፀም ለተጠቀሱት ቀበሌያት የታብሌት እና ሲምካርድ ስርጭት በማድረግ ወደ ተግባር በማስገባት የምዝገባውን ሥራ በድጅታል በማከናወን ላይ እንደሚገኙም ገልፀዋል ፡፡
ለእስካሁኑ ክንውንም ሆነ ለቀጣይ ተግባራት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው የገለፁት አቶ ሰለሞን የኩነቶች ምዝገባ ጠቀሜታን ለተለያዩ የገጠርና ከተማ ቀበሌያት የህዝብ ስብሰባ መድረኮችን፣ ትምህርት ቤቶችና ክበባትን በመጠቀም በተለያዩ መንገዶች የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከደቡብ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋር በመተባበር በአራት ቅርንጫፎች (በሚዛን ኤፍ ኤም ፣ ማሻ ኤፍ ኤም ፣ ቦንጋ ኤፍ ኤም ፣ ዋካ ኤፍ ኤም) የሬዲዮ አየር ሠዓት በመግዛት በተለያዩ ቋንቋዎች የባለድርሻ አካለትንና ማህበረሰቡን ተሳትፎን ማሳደግ የሚችል የግንዛቤ ስራ በማጠናከር ሽፋን እና ተደራሽነት እንዲስፋ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የተጀመረውን የዲጊታል ምዝገባ ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የተገልጋይ እርካታ ከፍ የሚያደርጉ ስትራተጂዎችን መዘርጋት ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫችን ነው ያሉት አቶ ሰለሞን ህብረተሰባችን እና ተቋማቶቻችንን ይበልጥ በማቀናጀት አፈፃፀሙ ዝቅ ያለበትን ሞትና ጉድፈቻ ምዝገባ የማላመድ ስራ በአፅንኦት እንሰራለን ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ዘንድሮ የፀደቀዉ የሲቭልና የቤተሰብ ምዝገባ አዋጅ 1370/2017 ተግባራዊ ለማድረግ በ6ቱ ዞኖች በተመረጡ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በፌዴራል ኢምግሬሽንና ዘግነት አገልግሎት ጋር በመሆን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በማጠናቀቅ ላይ እንደሆኑም አውስተዋል፡፡
ተቋማዊ ትስስርን በተመለከተ በክልላችን ከሚገኙ ቁልፍ ዘርፎች ባሻገር ከኢምግሬሽንና ዘግነት አገልግሎት እና ስታትስትክስ ኤጀንሲ ጋር ይበልጥ በመቀናጀት የመንግስታችን ዕቅድ የሆነችውን “ሁሉም ሰው የሚታወቅባትን ኢትዮጵያ እንገነባለን” ብለዋል፡፡
የኩነቶች ምዝገባ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያለው በመሆኑ ባለድርሻ አካላትና ተቋማት በተክኖሎጂ ተደግፈው በተደራጀ ዕቅድ ተመርተው ለዜጎቻችን ሁለንተናዊ ጥቅም ልንሰራ ይገባል ያሉት አቶ ሰለሞን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል 5ቱንም ኩነቶች በአቅራብያቸው ባለው መመዝገቢያ ቦታዎች ምዝገባ በማካሄድ ከምዝገባው የሚገኙትን መብቶች እንዲጠቀሙ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
