ቆይታ ከእኛ ጋር!

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በበጀት ዓመቱ ለተቋሙ የተሰጡ አበይት ተግባራትን የዕቅድ አካል በማድረግ ባለፉት 9 ወራት ስራዎችን ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ሲሰራ ቆይቷል ፡፡


ቢሮው ከሚሰራቸው አበይት ተግባራት አንዱ በክልሉ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን የመከላከልና የህግ ከለላ በማሰጠት የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከል እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ከክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት ወ/ሮ ገነት መኩሪያ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ !

መ/ኮ፡- ስምና ኃላፊነትዎን ቢገልጹልኝ ?
ወ/ሮ ገነት መኩሪያ፡- ወ/ሮ ገነት መኩሪያ እባላለሁ የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ

መ/ኮ፡- በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የሚባሉትን ቢገልጹልኝ ?
አካላዊ ጥቃት ፡-ድብደባ፣በሰውነት ክፍሎች ላይ ጉዳት ማድረስ፣ህጻናትን ከአቅም በላይ ስራ ማሰራት ፣በእሳት ማቃጠል፣አሲድ መድፋት ወዘተ ናቸው፡፡ ስነ-ልቦናዊ ጥቃት ፡- ስድብ፣ማንቋሸሽ፣ክብረን መንካት፣ለሴቶችና ህጻናት ዝቅተኛ ግምት መስጠት ፣ ጾታዊ፣-ጾታን መሰረት ያደረግ ማንኛውም ጥቃት፣በስራ ቦታ ፣በመኪና ውስጥ ሴትን መጎንተል፣አስገድዶ መድፈር፣ለከፋ፣ሴቶችንና ህጻናትን ለወሲብ ንግድ መጠቀም ፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቃት፡-ሴቶች የንብረት ባለቤት እንዳይሆኑ ማድረግ፣ንብረታቸውን እንዳይሸጡ እንዳይለውጡ መከልከል፣ንብረታቸውን መቀማት፣ሴቶች በኢኮኖሚ ዘርፍ እንዳይሳተፉ ማድረግ እነዚህና መሰል ጥቃቶች ናቸው፡፡
መ/ኮ፡- በክልሉ በ2017 በጀት አመት ባለፉት ስምንት ወራት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል ምን ምን ስራዎች ተከናዉኗል? ቢገልጽልኝ ?
በሴቶችና በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ከፍርድ ቤት፣ፖሊስ ኮሚሽን፣ከፍትህ ቢሮዎች ጋር የግብ ስምምነት በመፈራረም በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ፡፡ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በጋራ በመቀናጀት በአርብቶ አደር አካባቢዎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከመከላከል አንጻር ለሚመለከታቸው የሴቶች፣ህጻናት፣ወጣቶችና ማህበራዊ ተቋማት ፣የፖሊስ ተቋም፣የፍትህ ተቋምና የጸጥታ ተቋም አመራሮችና ባለሙያዎችን የአቅም ግንባት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ከሚመለከታቸው መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት በተለይ ከአክሽን ኤድ ኢትዮጵያ ሚዛን ቅርንጫፍ፣ከዩኒሴፍ ኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
የሴቶችና ህጻናትን የጥቃት ተከላካይ ኮሚቴዎችን ማዋቀርና ማሰልጠን ስራ ተሰርቷል ፣ ከፍትህ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ፡፡ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤና የንቅናቄ ስራዎች ተሰርተዋል ፡፡ በአለም አቀፍ የሴቶች ቀን፣16ቱ የጸረ-ጾታን ቀን፣የአለም የህጻናት ቀንን መነሻ በማድረግ የህዝብ ንቅናቄ ስራዎች በስፋት ተሰርተዋል፡፡ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችና ህጻናት የህግና የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል
መ/ኮ፡- በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማህበረሰቡ በምን መልኩ መከላከል ይችላል ቢያብራሩልኝ?
ጥቃት አድራሾችን አጋልጦ ለህግ ሲያቀርብ ፣ በጥቃት ተከላካይ ኮሚቴዎች ውስጥ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል አንዱ የማህበረሰብ ውይይት ማድረግ ስለሆነ በውይይታቸው ስለ ሴት ልጅ ጥቃት እንዲወያዩ በማድረግ ፣ በሴቶችና በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን አይቶ ዝም ላለማለት፣ላለመፈጸም ቃል እንዲገቡ በማድረግ ፣ የአደረጃጅት መዋቅሮችን ማጠናከር፣ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እነዚህን ተግባራት በማከናወን በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማህበረሰቡ መከላከል ይችላል፡፡
መ/ኮ፡- ጥቃቱ የደረሰባቸዉ ሴቶችና ህጻናት ከፍትህና ከስነ_ ልቦና አኳያ ምን አይነት ስራዎች እየተሰሩ ነዉ ?
በአንድ ማዕከል የተሟላ አግልግሎት እንዲያገኙ በሚዛን አማን ቲችግ ሆስፒታል አንድ የተሀድሶ ማዕከል ተቋቁሞ ጅምር ስራዎች መኖሩ ፣ አጥፊዎች/ወንጀለኞች/ ወንጀል ፈጽመው ሲገኙ በህግ እንዲጠየቁ ከፍትህ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ፣ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህጻናት የህክምና፣ህግ፣የስነ-ልቦና ድጋፍ ተደርጓል ፡፡ ከፍትህ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡
የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት ራሱን ታለ ግንባታና የራሱ ይሆነ ሶሻል ወርከር ጭምር የሚያስፈልገው ጉዳይ ስለሆነ ገና ሰፊ ስራ ይጠበቅብናል
መ/ኮ፡- በሴቶችና ህጻናት ጥቃቶች ዙሪያ ከመከላከል አንጻር የባለድርሻ አካላቱ ተሳቶፎ እንዴት ያዩታል? ቢያብራሩልኝ?
ባለድርሻ አካላት የሴቶችንና የህጻናትን ጥቃት ለመከላከል በስልጠናና አቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በማሳተፍ እና አብሮ በመስራት በጀት መድበው እንዲሰሩ መደረጉ ፣ ሴቶችና ህጻናት ማንኛውም ጥቃት በሚደርስባቸው ጊዜ ለጉዳዩ ባለቤት በመሆን የተጣለባቸውን ኃላፊነቶች እየተወጡ መሆኑ
ጥቃቶችን አጋልጦ ለህግ የማቅረብ፣ምስክር የመሆን ስራዎች በተገቢው ይሰራሉ፣ ነገር ግን ተግባሩ የኔ ጉዳይ ነው ብሎ ከመፈፀም አኳያ በታችኛው መዋቅር ከመዋቅር ልዩነቶች አሉ፡፡ቀጣይ የድጋፍና ክትትል ስርዓትን በማጠናከር ለውጥ እንዲመጣ እንሰራለን
መ/ኮ፡- ከህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተሰሩ ተግባራት አሉ ? ቢያብራሩልኝ
ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው ወደ ክልላችን የሚመጡ ህጻናትን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ ተደርጓል ፡፡ የልማት ድርጅቶች ህጻናት አቅማቸው የማይፈቅደውን በጉልበት ስራ እንዳያሰሩ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ፣ ከአሰሪዎች በተለይ ከአሰሪ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር ተቀናጅቶ የመስራት /በተለይ ከተማዎች ላይ/ ፣ ስለ ህጻናት መብቶች በተመለከተ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማመቻቸት ስለ ህጻናት መብቶች ያላቸውን እውቀት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ በማድረግ
መ/ኮ፡- ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ከማስቀረት አኳያ የተሰሩ ስራዎች ካሉ ቢገልጹልኝ?
በተለይ የሴት ልጅ ግርዛትንና ያለእድሜ ጋብቻ ለማጥፋት ግብ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን በካፋና ዳውሮ ወረዳዎች በዩኒሴፍ የገንዘብ ድጋፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ፡፡በካፋ ዞን በጊንቦ ወረዳ የሴት ልጅ ግርዛት በተመለከተ ምርጥ ተሞክሮ ተቀምሯል ፡፡ከሀይማኖት አባቶች ጋር በቅንጅት ስራዎች እንዲሰሩ ተደርጓል ፡፡በሰቆጣ ቃል ኪዳን ማስፋፊያ ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ በክልላችን በሁሉም ዞኖች በ11 ወረዳዎች ያለ እድሜ ጋብቻን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው ፤የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመቀነስ የግንዛቤ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ፤ ይህ ተግባር በሁሉም አከባቢዎች ለመከላከልና ለማስቀረት መደበኛ የዕቅዳችን አካል በመሆኑ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ ይገኛል፡፡
መ/ኮ፡- ቀረ የሚሉት ጉዳይ ካለ ?
ወ/ሮ ገነት መኩሪያ ፡- ለመላው የክልላች ህዝብ የማስተላልፈው ጤናማ ዜጋ ፣ቤተሰብ እና ቀጣይ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት በሴቶችና በህፃናት ላይ ሚደርሰውን ጥቃት ቀድሞ የመከላከል ስራዎችን በየደረጃው ካላው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ተቋማትጋር በጋራ በመስራት ችግሩን ለመቅረፍ ከጎናች እንዲሆኑና ከመከላከል አልፎ ጥቃት አድርሶ ሲገኙም ፍትህ ለማግኛት ትክክለኛ መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩን መለዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡
መ/ኮ፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ ፡፡
ወ/ሮ ገነት መኩሪያ ፡- እኔም አመሰግናለሁ ፡፡
በፀሀይ በላቸው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *