





የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት የህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ለዞንና ወረዳ የህብረት ሥራ ኦዲተሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በሚዛን አማን ከተማ እየሰጠ ይገኛል።
የስልጠና መድረኩ ከካልም ፕሮግራም ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን ”በህብረት ሥራ ኦዲቲንግ እና በህብረት ሥራ ኦዲት አፈጻጸም መምሪያ ቁጥር 978/2016 ዙሪያ ያተኮረ ነው።
በክልሉ የህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቀበሌ መንገሻ ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት፤ መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት ትርፋማ ስለመሆናቸው እና የሚያጋጥሙ ክሳራቸውን መለየት እንዲሁም በኦዲት የተገኘው እዳ እየመለሱ እንዲሄዱ የማህበራት ኦዲተር ባለሙያዎች ሚናቸው ከፍተኛ ነው።
በክልሉ በካልም ፕሮግራም ከ2መቶ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ተሳትፎ ተፋሰስ ልማት የተደራጁ የህብረት ሥራ ማህበራት እንዳሉትም አቶ ቀበሌ መንገሻ ጠቁመዋል።
በየዓመቱ ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጋር በመተባበር የህብረት ሥራ ማህበራት ኦዲት ባለሙያዎች አቅም የመገንባቱ ሥራ ይሰራል ያሉት አቶ ቀበሌ መንገሻ፤ ዛሬ ከካልም ፕሮግራም ጋር በመቀናጀት ለዘርፉ ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠና የዚህ አካል ነውም ብለዋል።
የህብረት ሥራ ማህበራት የኦዲት አገልግሎት በብቃትና በጥራት ማከናወን ለማህበራት ደህንነት ጥበቃ ድርሻው የጎላ መሆኑን ነው አቶ ቀበሌ መንገሻ ያብራሩት።
በክልሉ በካልም ፕሮግራም የተደራጁ የህብረተሰብ ተሳትፎ ተፋሰስ የህብረት ሥራ ማህበራት እያከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች ውጤታማነታቸውን ለማረጋገጥ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ዙር የድጋፍና ክትትል ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
በተደረገው ድጋፍና ክትትል በፕሮግራሙ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች፣ ገንዘብ አመላለስ እንዲሁም የማህበራት አባላት ለሥራ ያላቸው መነሳሳት ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉንና ለዚህም የዘርፉ ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበርም ጠቅሰዋል።
በክልሉ የሚገኙ መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት ህይወት ኖሮአቸው ቀጣይነት ባለው መልክ ወደ ዩንኤን እንዲያድጉ ከሥር ጀምሮ ማብቃትና የመደገፍ ሥራ በትኩረት እንደሚሰራም በንግግራቸው አረጋግጠዋል።
በህብረት ሥራ ኦዲቲንግ እና ህብረት ሥራ ኦዲት አፈጻጸም መምሪያ ቁጥር 978/2016 ዙሪያ የሚሰጠውን ስልጠና የዘርፉ ባለሙያዎች በተገቢው በመከታተል እርስ በእርስ ልምድ በመለዋወጥ እና ግልጸንነት በመፍጠር እንዲሁም ታች ያሉ ባለሙያዎች አቅም በመገንባት ማህበራትን የማብቃት ሚና እንዲወጡም አሳስበዋል።
የማህበራቱ ሥራ አፈጻጸም በየጊዜው መከታተል፣ ትርፍና ክሳራቸውን እያረጋገጡ እንዲጓዙ መደገፍ ያስፈልጋልም ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
በኦዲት የተገኙ ዕዳዎችን በወቅቱ አለመመለስ ለማህበራት መበታተን ዋነኛ መንስኤ በመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች በኦዲት የተገኘው እዳዎች እንዲመለስ ሚናቸውን በተገቢው እንዲወጡም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የህብረት ሥራ ማህበራት አደረጃጀትና አፈጻጸም ውጤታማ ሆነው የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ የማህበራት አደራጅ ዘርፍ፣ የምርት ግብይትና ግብዓት እንዲሁም ኦዲት ዘርፍ ጥምረት ቀልጣፋና ብቃት ያለው አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በስልጠና መድረኩ በክልሉ ግብርና ቢሮ የካልም ፕሮግራም ESMS SPECIALIST ባለሙያ በሆኑት አቶ ኬሮ ከበደ ስለካልም ፕሮግራም አመጣጥ ዙሪያ የተዘጋጀ ሰነድ አቅርበዋል።
በተጨማሪም በክልሉ የህብረት ሥራ ልማት ኤጀንሲ የማህበራት ደህንነትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አድራሮ በህብረት ሥራ ኦዲት አፈጻጸም ዙሪያ የተዘጋጀ ስልጠና ለዘርፉ ባለሙያዎች እየሰጡ ይገኛሉ።
በፍቅር ከበደ
