




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ከምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) ጋር በመቀናጀት በድልድይ እና መንገድ ልማት ለተሰማሩ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መድረክ በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ የስልጠና መድረኩን ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት ክልሉ በአዲስ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ የህዝቡን መሰረተ ልማት ፍላጎት ለሟሟላት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መቆየቱን ተናግረው የተጀመሩ መሠረተ ልማቶች እንዲጠናቀቁ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ያስፈልጋል ብለዋል።
በመንገድ ልማት ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን አቅም መገንባት ጥራት ላለው ስራ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉት ወቅት እንደገለፁት የመሰረተ ልማት ችግር ዋነኛ የህዝቡ መልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን ተናግረው የክልሉ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በውይይቱ የዞንና ክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከክልሉ የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆናቸዉን የሸካ ዞን ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
