
ያለፉት 7 የለውጥ ዓመታት ዜጎች የሀገራቸው የፓለቲካ ጉዳይ ላይ ያለከልካይ መሳተፍ አለባቸው የሚለውን እሳቤ ያመጣ ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍና የሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለፁ።
ለውጡ የአጋር እና የዋና ፓርቲ ክፍፍልን በማስቀረት ህብረ ብሄራዊ፤ ሀገራዊ ፓርቲ በመመስረት ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
ሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን የፓለቲካ ችግር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ እየተደረገ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ጥሪውን ተከትሎም ትልቅ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የፓለቲካ ታሪክ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ገብተው የፓለቲካ ተግዳሮቶችን በጋራ እንዲፈቱ በሀገር መሪ ጥሪ ሲቀርብላቸው የመጀመሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ጥላ ስር ተሰባስበው የፓለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ዜጎች 16 ሚሊዮን እንደሚጠጉም አንስተዋል።
የመደመር እሳቤ ልዩ መገለጫው ትስስር ነው ያሉት ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፤ የፓለቲካ ልዩነቶች ቢኖሩም ሀገር እና ህዝብን የሚመለከቱ የጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመተባበር እንችላለን የሚል እሳቤን የያዘ ነው ብለዋል።
በሀገራችን ውስጥ ያሉ የፓለቲካ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ አፍራሽ ኃይሎች ጫና ስር በወደቀች ጊዜ ሀገርንና ህዝብን አስቀድመው የፓለቲካ ልዩነትን ወደ ጎን በመተው የሀገር ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ በጋራ ቆመዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልፀው፤ ይህም ዋና ዋና የሚባሉ የሀገር አጀንዳዎች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ እና አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚያስችል የጋራ መድረክ መፍጠሩን አክለዋል።
የኢትዮጵያ የፓለቲካ ስብራት እንዲጠገን ተቋማዊ እና ባህላዊ መሠረት ያለው የዲሞክራሲ ስርዓት መገንባት ላይ ልዩ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑንም ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገልፀዋል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
