




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመጀመሪያው የኾነው የሚዛን አማን ማዕከል፤ መሶብ የአንድ ማዕከል አግልግሎት ተመርቀው ለአግልግሎት በቅቷል።
በማዕከሉ ምርቃት ስነስርዓት ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹት፥ መንግሥት ዜጎች ያማረሩ የአግልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።
በዚህም መሠረት በሚዛን ከተማ በክልሉ መንግሥት ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የበጀት ድጋፍ ተገንብተው ለአግልግሎት የበቃው መሶብ የአንድ ማዕከል የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያሳልጥ መኾኑን ጠቁመዋል።
የመንግሥት አግልግሎት አሰጣጥን ከብልሹ አሰራር የማጽዳት ተግባር በየደረጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንሼቲቭ የኾነው መሶብ የአንድ ማዕከል፤ ቀልጣፋ አግልግሎት ለዜጎች በማቅረብ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላል ብለዋል።
መሰል የአንድ ማዕከል አግልግሎት በክልሉ አምስት ከተሞች በተያዘው ተግባራዊ እንዲኾን መግባባት መፈጠሩን የገለጹት ዶ/ር ነጋሽ፥ በተላይም በታችኛው መዋቅር ህዝብን ለምሬት የዳረጉ ከማዘጋጃ ቤታዊ አግልግሎት እና ከግብር ጋር የሚገናኙ አግልግሎት አሰጣጥ ያሻሽላል ብለዋል።
ማዕከሉ ከዛሬ ጀምሮ በሚዛንና አከባቢው ለሚገኙ ተገልጋዮች ተገቢውን አግልግሎት እንደሚሰጥ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ የከተማው መንግሥትና ህዝብ ማዕከሉ ቀጣይነት ያለውን አግልግሎት እንዲሰጥ እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
መሶብ የሰው ተኮር አግልግሎት ልህቀትን በማረጋገጥ ለዜጎች ክብር ተገቢውን ስፍራ የሚሰጥ እንደኾነ የገለጹት የሲቪል ሰርቪስ ምክትል ኮሚሽነር አልማዝ መለሰ፥ ማዕከሉ ዜጎች ከመንግሥት የሚፈልጓቸውን በአንድ ቦታ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
የመሶብ አንድ ማዕከል አግልግሎት ለተገልጋዮች ፍትሀዊ፣ ፈጣንና ተጠያቂነት የሰፈነበት አግልግሎት በመስጠት ዜጎችንና መንግሥት የሚያቀራርብ ትልቅ ስኬት እንደኾነም አንስተዋል።
ማዕከሉ በርካታ ተግባራት በአንድ አቀናጅተው የዜጎችን ጊዜና ጉልበት የሚታደግ እንዲሁም የመንግሥት አግልግሎት አሰጣጥ የሚያሳልጥ እንደሆነም ነው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው የገለጹት።
የማዕከሉ ግንባታ በአጭር ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቃ የክልሉ መንግስት ለሰጠዉ አመራር ምስጋና ያቀረቡት የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን፤ የማዕከሉ መገንባት የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ውጤታማነት ያሳያል ብለዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
