





የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ የጤና ቢሮ “ዘላቂ እንቨስትመንት እና ፈጠራ ለጤናው ዘርፍ እምርታ” በሚል መርህ ቃል የጤና ሴክተር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፥በጤናው ዘርፍ የተለዩ የገጠር ትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎችን በመፈጸም የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ ማሻሻል ይገባል ብለዋል።
የገጠር ትራንስፎርሜሽን፣ የገጠሩን ማኅበረሰብ አጠቃላይ ኑሮ ለማሻሻል ፈጠራና ፍጥነት እንዲሁም አንዳንድ ተግባራትን በዝላይ መፈጸም እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
በገጠሩ የኑሮ መሠረት ከሆነው የግብርናው ዘርፍ ባሻገር በጤናው ዘርፍ የተጀማመሩ አበረታች ተግባራት መኖራቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳደሩ ይህንን ተግባር በማጠናከር እምርታዊ ለውጥ ማስመዝገብ ይገባል ብለዋል።
በገጠሩ፥ በቤተሰብ ደረጃ የኑሮ ሁኔታን በማሻሻል የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ፤ የግልና የአከባቢ ንጽሕናን ማስጠበቅ እንዲሁም በኅብረተሰብ ዘርፍ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የጠቆሙት።
የጤና ተቋማት ሁለንተናዊ ገጽታና የአግልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በመቅረፍ ዜጎች የተሻለ የህክምና አግልግሎት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ማስቻል እንደሚገባ ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የሚጠበቁ ውጤቶች እንዲመዘገቡ የጤናው ዘርፍ አመራሮች ቁርጠኛ ያስፈልጋል ብለዋል።
በአምቡላንስ አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራር ለማረም የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በጤና ኤክስቴንሽን ስርዓት የተጠያቂነት አሰራር መዘርጋት አለበት ብለዋል።
በማዐጤመ እና በመድሀኒት አስተዳደር ዘርፍ የመጣውን አውንታዊ ለውጥ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ያስገነዘቡት ርዕሰ መስተዳድሩ የወረርሽኝ መከላከል ስራው በቅንጅት መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።
የጤና ዘርፍ የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ማሻሻል እንደሚገባ ያስገነዘቡት የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም፥ የገጠር ትራንስፎርሜሽን እንዲሳካ የጤናው ዘርፍ አመራር በቁርጠኝነት መስራት አለበት ብለዋል።
በክልሉ የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ለማሳካት መጠነ ሰፊ ተግባራት እየተከናወነ መኾኑን የሰው መለከቱት አቶ ኢብራሂም በተላይ ጽዱ አከባቢን ለመፈጠር በትኩረት እየተሰራ እንደኾነ ጠቁመዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን በክልሉ በሀገር ደረጃ ምሳሌ የኾነ ተግባር መፈፀሙን የገለጹት ኃላፊ በዚህም ዓመትም ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
