
የነፃ ምርት ዝውውርን ማስፈን የኢኮኖሚ ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነዉ።
የክልላችን ብልጽግና የሚረጋገጠው በሕግና በሥርዓት በተመራ ነፃ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲኖር ነዉ።
በሀገራችን ነጻ የምርት ዝዉዉርን የሚገቱ በየአካባቢዉ የተቋቋሙ ኬላዎች እንዲነሱ መንግስት መወሰኑ ይታወቃል።
መንግሥት የወሰነውን ይህንን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ውሳኔ መሠረት በማድረግ፣ በየአካባቢው ተቋቁመው ነፃ የምርት ዝውውርን የሚያደናቅፉ ሕገ-ወጥ ኬላዎች ሁሉ እንዲነሱ መደረግ እንዳለበት ይታወቃል። ይህ እርምጃ አርሶ አደሩና ነጋዴው ያመረተውን ምርት ያለአንዳች እንቅፋትና ተጨማሪ ወጪ በቀጥታ ለገበያ እንዲያቀርብ በማስቻል የክልላችንንና የሀገር አቀፍ ኢኮኖሚን የማሳደግ ዓላማ ያለዉ ነው።
ይህ ወሳኝ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያሳልጥ አሠራር በክልላችን አንዳንድ አካባቢዎች ወጥ በሆነ መንገድ እየተተገበረ አይደለም። ይህም ምርት በነፃነትና በተቀላጠፈ ሁኔታ ለገበያ እንዳይቀርብ በማድረግ፣ ዜጎች በሥራቸዉ ልክ እንዳይጠቀሙ እንቅፋት ሆኗል። ይህ መዘግየት በክልላችን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑም ግልጽ ነው።
ይህንን ኢኮኖሚን የሚያዳክም አሰራር ሙሉ በሙሉ ለማስቆም፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት “ለታክስ”፣ “ለቀረጥ” እና “ለአካባቢ ልማት” በሚል ሽፋን በየሰፈሩና በመንገድ ዳር የተቋቋሙ ሕገ-ወጥ ኬላዎች በሙሉ መነሳት እንዳለባቸዉ ወስኗል።
የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል እና ለጸጥታ ሥራ አጋዥነት በሚታወቅ የክልሉ ወይም የፌዴራል አካል ተፈቅደው፣ በግልጽ አሰራር የሚመሩ ኬላዎች ብቻ ተግባራቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል።
ይህንን የክልሉ ዉሳኔ በተገቢው ጊዜ ውስጥ ተቀብሎ ወደ ተግባር የማይለውጥ ማንኛውም የመንግሥት መዋቅር፣ የሥራ ኃላፊ፣ ወይም ተዋናይ አካል ተጠያቂነቱን ይወስዳል! ክልሉ ለነፃ ገበያ እና ለሕግ የበላይነት ያለውን ቁርጠኝነት ለማስፈጸም አስፈላጊውና የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን በይፋ እናሳውቃለን።
የምርት አዟዟሪዎችና አሽከርካሪዎች በህገወጥ ኬላዎች የሚደርስባችሁን እንግልት እና ህገወጥ ክፍያን በተመለከተ ይህንም እንዲያስተባብር ኃላፊነት ለተሰጠው የመንግሥት አካል በስልክ ቁጥር +251969303332 መረጃ መስጠት የምትችሉ መሆኑን እናሳውቃለን።
