
በክልሉ በ3 ዓመታት ዉስጥ በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎና ከአጋር አካላት በተገኘ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ከ1ሺ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ መስራት መቻሉን አቶ ፋጂዮ ሳፒ ተናገሩ።
የ122 ኪሎ ሜትር የአዲስ መንገድ እና ጥገና ስራ በቅርቡ እንደሚጀመርም ኃላፊው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደጠቆሙት አዲሱ ክልል በተመሰረተ ማግስት ቁልፍ የመሰረተ ልማት ችግሮችን በመለየት ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
በተለይም በቀድሞ ክልል በቀበሌ ተደራሽ 5 እና በገጠር መንገድ ስራዎች 18ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ድልድዮችን በመጨረስ ለትራፊክ ክፍት ሚድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
እንደ ክልል ባለፉት 3 አመታት 36 የመንገድ ፕሮጀክቶችን መስራት መቻሉን ገልጸው በክልሉ መንግስት በ500 ሚሊየን እንዲሁም ከፌደራል መንገድ ፈንድ በተገኘ 300 ሚሊየን ብር በጀት 440 ኪሎ ሜትር መንገድ የተሰራ ሲሆን ከህብረተሰቡ ተሳትፎ በተገኘ 545 ሚሊየን ብር 628 ኪሎ ሜትር መንገድ መሰራቱን ገልጸዋል።
በቅርቡም ከፌደራል መንግስትና ከአለም ባንክ በተገኘ የበጀት ድጋፍ በ6 ዞኖች ውስጥ ለሚገኙ 6 ወረዳዎች 51 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድና 71 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ስራ ለመስራት የጨረታ ስራው መጠናቀቁን ገልጸዋል። በዚህም መኤኒት ጎልዲያ ፣ ሼይ ቤንች ፣ የኪ ፣ አዲዮ ፣ ኢሰራና ኮንታ ኮይሻ ወረዳዎች በመሰረተ ልማቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።
ዘመናዊ መናኸሪያና ትራንስፖርትን በክልሉ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የሚዛን አማን ፣ ቦንጋ እና ታርጫ ዘመናዊ የመናኸሪያ አገልግልግሎትን ለማስፋት የግንባታ ስራዎቹ እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ለ3 መናኸሪያዎች ግንባታ የክልሉ መንግስት ከ249 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መያዙን የገለጹት አቶ ፋጂዮ የ3 ግንባታ ከ2 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከኮንትራክተሮች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
አቶ ፋጂዮ በጋዜጣዊ መግለጫቸው በፌደራል መንግስት እየተሰሩ ከሚገኙ መንገዶች መካከል የሚዛን ቴፒ ፣ ማሻ ጎሬ ፣ ከጂማ ጪዳ ያሉ የመንገድ ስራዎች እየተፋጠኑ ሲሆን የሺሺንዳ ቴፒ የመንገድ ስራ አሁንም ችግር ውስጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተለይም በአንዳንድ ፕሮጀክቶች የተቋራጮች አቅም ማነስ እና የአማካሪዎች ችግር በሰፊው መታየቱን ገልጸው የዲሪ ማሻ መንገድ ጨረታ ቢወጣም ተቋራጭ ባለመቅረቡ መዘግየቱን ገልጸዋል።
