




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን በካፋ ዞን ገዋታ ወረዳ የቦጊንዳ የሻይ ችግኝ ዝግጅት ጣቢያ ከአካባቢው ለተወጣጡ አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቷል።
ዓላማው የተዘጋጀውን የሻይ ቅጠል ችግኝን ከተከላ በፊት ከውጪው አየር ጋር በተገቢ ማላመድ፣ የመንከባከብና ከተላመደ በኃላ ወደ አርሶ አደሩ ማሳ በመውሰድ ለመትከል ከማሳ ልየታ እስከ ተከላና ምርት አሰባሰብ ሂደት ላይ ግንዛቤ ለማስጨጥ የተዘጋጀ ስልጠና ነው።
በተግባር የተደገፈ ስልጠናው በውሽውሽ የሻይ ልማት ባለሙያ በሆኑት በአቶ ጋዲሳ ተስፋዬ ለሰልጣኞች ተሰጥቷል።
በስልጠናው ችግኙን በአግባቡ የማላመድ ሂደቱ በአግባቡ መተግበር የችግኞችን ሞት እንደሚታደግ እንዲሁም ተገቢውን ግብዓትና ጥንቃቄ ማድረግ ለምርታማነት ሚናው የጎላ መሆኑ ተነስቷል ።
መድረኩን ያጠቃለሉት የክልሉ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ፣ የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ዕውን ለማድረግ በአካባቢው ያለውን ዕምቅ አቅምን በመለየት ወደ ውጤት በመቀየር ከአካባቢው ፍጆታ አልፍ ለማዕከላዊና ውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ማምረት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከነዚህም አንዱ በክልሉ የተጀመረው የሻይ ቅጠል ኢንሼቲቭ መሆኑን በመጥቀስ በዞኑ ውስጥ ያለው ተስማሚ የአየር ንብረት፣ የዝናብ ስርጭትና ለምና ተስማሚ መሬትን በተገቢው በመጠቀም ለተጠቃሚነት በትኩረት በዕቅድ መስራት አለበት ብለዋል።
አክለዉም መንግስት እንደ ቡና ልማት ሁሉ ለሻይ ልማቱ ሥራ ትኩረት በመስጠት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ያነሱት አቶ አስራት ከሂደት እስከ ውጤት ያለው ድካም የሚጠይቅ በመሆኑ ለተሻለ ውጤት በትዕግሥት መስራት እንደሚገባው አንስተዋል።
ለተከላ የሚመረጠው ማሳ ለኢንዱስትሪው የሚመች፤ በኩታ ገጠም በማልማት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በቅንጅት መስራት ይገባል ያሉት የክልሉ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጅአብ ናቸው።
ስልጠናውን በግብዓትነት በመጠቀም ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ በመፍጠር ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጨምረው ተናግረዋል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የገዋታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አርጋው ኃይሌ፤ የክልሉ ግብርና ቢሮ በወረዳው የተጀመረው ኢንሼቲቭ ውጤታማ እንዲሆን ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ስልጠናው ኢንሼቲቩ አድስ እንደመሆኑ መጠን የነበሩ የግንዛቤና የክህሎት ክፍተት እንደሚሸፍን ሰጣኞቹ አንስተዋል።
በስልጠናው ላይ የክልሉ ቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጅአብን ጨምሮ ተከላ ከሚካሄድባቸው 8 ቀበሌዎች የመጡ የቀበሌ ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የግብርና ባለሙያዎችና የችግኝ ጣቢያ አስተባባሪዎችና የባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በጌታሁን ግርማ
