




በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም እና ህብረተሰቡን በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው የሰንበት ገበያ፣ በሁለቱም ማዕከላት (ሚዛንና አማን) በልዩ ትኩረት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ።
የከተማ አስተዳደሩ የሰንበት ገበያን ዘላቂና ምቹ ለማድረግ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሰ ይገኛል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ በሚዛንና በአማን ለሚገኙ የገበያ ማዕከላት ከ2.8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግዙፍ የገበያ ድንኳኖች ግዥ ተፈጽሞ ወደ ስራ መገባቱ ተረጋግጧል።
ይህም ነጋዴዎችና ሸማቾች ከአየር ንብረት ተጽዕኖ ነፃ በሆነ መልኩ ግብይት እንዲፈጽሙ አስችሏል።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታቸው ታቻ እንደገለጹት፤ የሰንበት ገበያው ዋና ዓላማ በአምራችና በሸማች መካከል ያለውን ያልተገባ የደላሎች ጣልቃ ገብነት ለማስቀረት፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ከኑሮ ውድነት ለመታደግና የመረጋጋት መንፈስ ያለው የገበያ ስርዓት ለመፍጠር ነው ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በተለይ የከተማ ከንቲባና የፓርቲ ጽህፈት ቤት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት በጀት በመመደብና ክትትል በማድረግ ላደረገው አስተዋጽኦ ሃላፊው ምስጋና አቅርበዋል።
የጽህፈት ቤቱ የሸማች የስራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ሄኖክ በላቸው በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት በገበያው ላይ በስፋት የግብርና ምርቶች እየቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል።
አክለውም፣ በቀጣይ የህብረተሰቡን ፍላጎት ይበልጥ ለማርካት የፋብሪካ ምርቶችን (እንደ ዘይት፣ ስኳርና ዱቄት ያሉ) በስፋት ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በሰንበት ገበያው ላይ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች በስፋት እየተሳተፉ ይገኛሉ። እነዚህ ወጣቶች ምርቶችን በቀጥታ ከአምራቾች በመረከብ ለህብረተሰቡ እያቀረቡ ሲሆን፣ ይህም ለወጣቶቹ የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ ለሸማቹ ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገኝ አድርጓል ተብሏል።
የሰንበት ገበያው የዋጋ ልዩነት ያለው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ከተለመደው ገበያ ጋር ሲነጻጸር በእያንዳንዱ ምርት ላይ ከ5 እስከ 15 ብር የሚደርስ ቅናሽ እንዳለውና የሚቀርቡት የግብርና ምርቶች ትኩስና ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ናቸው ሲሉ ያነጋገርናቸው ሸማችች ገልጸዋል።
አስተያዬ ሰጪዎቹ አክለውም የገበያ ቦታዎቹ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በቀላሉ ሊደርሱባቸው በሚችሉ አማካኝ ቦታዎች ላይ መቋቋማቸው ትልቅ እፎይታ ሰጥቷል።
የሰንበት ገበያ በአሁኑ ወቅት የመንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እየተሰራበት ያለ ተግባር ነው። በሚዛን አማን ከተማም ይህ ተግባር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታ ተጠቃሚ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀጣይም የግብይት ሰንሰለቱን በማዘመን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል ሲል የከተማው ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።
