በዕውቀት፣ በክህሎትና በስነ ምግባር የታነፀ የፖሊስ አመራሮችና አባላትን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ከፌደራል ፖሊስ እና ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩንቨርስቲ ጋር በመቀናጀት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለሚወስዱ አመራሮች በቦንጋ ከተማ ስልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

በሰላም ማስከበር ስልጠና ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰብስቤ ሻዌኖ የህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ዕውቀትና ስነ ምግባርን የተላበሰ ፖሊስ እና ዘመናዊ የፖሊስ ተቋምን ለመገንባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዘመናዊ ፖሊሳዊ አገልግሎት ለመስጠት ዘመኑን በሚጠይቀው ልክ ራሱን በዕውቀት በክህሎትና በስነ ምግባር የታነፀ ፖሊስ ለማፍራት የክልሉ ፖሊስ ኮምሽን በአጭር፤በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን በማዘጋጀት አባላቱን ብቁ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በየደረጃው ክፍተቶችን በመለየት ከፌደራል ፖሊስ እና ከሌሎች በክልሉ ከሚገኙ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር የፖሊስ አመራሮችና አባላትን አቅም በስልጠና በመስጠት አቅማቸው እየገነባ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ኮምሽነር ሰብስቤ አክለው በአለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ሂደት ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ አልፎ በአለም አቀፍ ደረጃ ሰላምን በማስከበር ትልቅ ልምድ እንዳላት ጠቁመው በዚህ አለም አቀፍ ሰላም ማስከበር የክልላችን የፖሊስ አመራሮች የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እና ስምሪት ለመስጠት እንዲቻል በተዘጋጀው በስልጠና ማለፍ እንደሚገባቸውና ሰልጣኞች ስልጠናውን በብቃት በመከታተል ለሚሰጣችሁ ተልዕኮ ራሳችሁን ዝግጁ እንድታደርጉ አሳስባለሁ በማለት ስልጠናውን በይፋ አስጀምረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፌደራል ሰላም ማስከበር ኃላፊ ኮማንደር ተገኝ አጋዥ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባለፋት አመታት በዕዉቀት በክህሎትና በሙያ ስነ ምግባር የተካነ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችል የፖሊስ አባላትን በማሰልጠንና ወደ ስራ በማሰማራት ጉልህ ሚና እየተወጫወ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩንቨርስቲ የሀገሪቱን የፖሊስ ሚና ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በዕውቀት፣በክዕሎት እና በሥነ-ምባር የታነፀ የፖሊስ አመራርና ባለሙያ ማፍራት ተቀዳሚ ተግባር በማድረግ የተለያዩ አጫጭር የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት የፖሊስ አገልግሎት ለማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋፆኦ እያደረግ እንደሚገኝ ያመለከቱት ኮማንደር ተገኝ የፌደራል ፖሊስ በሰላም ማስከበር የክልል ፖሊስ አመራሮችን እና አባላትን በሰላም ማስከበር ስልጠና ስምሪት ለመስጠት ስልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ሀብታሙ መላኩ ስልጠናው ለተከታታይ 12 ቀናት የሚሰጥ ሲሆን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ስር ካሉ 6 ዞኖች እና ከክልሉ ፖሊስ ኮምሽን የተወጣጡ 42 የፖሊስ አመራሮችና አባላት ስልጠናው እየውዱ እንደሚገኝ ተናግረዋል ሲል የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *