በክልሉ ህጋዊ ሰውነት ኑሯቸው ከሚንቀሳቀሱ ሀገራዊም ሆነ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀናጅቶ እየተሰራ ያለውን ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፦ አቶ ፍቅሬ አማን

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤና የቀጣይ አቅጣጫ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት የብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን እንደገለፁት በሀገራችን ያሉ የፓለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር ሠላም፣ልማት ፣አብሮነት፣ የጋራ የሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመስራት ይዘውት የተነሱበትን ዓላማ ለማሳካት መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።

በሀገር በቀል የፖለቲካ እሳቤዎችን በመያዝ ልዩነት ላይ በሰለጠነ መንገድ መወያየት አለብን ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ፉክክር ጤናማ ሊሆን እንደሚገባው አቶ ፍቅሬ ጠቁመው በልዩነት ውስጥ አንድነትን ፣በአንድነት ውስጥ ልዩነት እንዳለ በውል መገንዘብ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ ህጋዊ ሰውነት ኑሯቸው ከሚንቀሳቀሱ ሀገራዊም ሆነ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተቀናጅቶ እየተሰራ ያለውን ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ፍቅሬ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፕረዚዳንት አቶ ሰለሞን አየለ እንደገለፁት የፓለቲካ ፓርቲዎች በሀገራችን ዋስትና ያለው እውነተኛ ዲሞክራሲ እውን እንዲሆንና የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ እንዲጎለብት፣ ዘላቂ ሠላም እና መረጋጋት በማስፈን ልማት እንዲረጋገጥ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ ተመስርተው የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጋቢት 5/2011 ዓ.ም የቃል ኪዳን ሰነድ ተፈራርመው የጋራ ምክር ቤት መቋቋሙን ተናግረዋል ።

የፖለተካ ፓርቲዎች በተናጥል ያላቸውን የፖለቲካ ፍላጎት እውን ለማድረግ ከሌሎች የፖለቲካ ፖርቲዎች ጋር በትብብር መስራት ውጤታማ እንደሚያደርግ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ከተመሰረተ ጀምሮ አደረጃጀቱን እና አሰራሩን በየጊዜው በማስፋት እና በማሻሻል እስከ ወረዳ ቅርንጫፍ በመክፈት በመክፈት በመላው ሀገራችን በመንቀሳቀስ ሰፊ ሥራዎች እየሰራ ነው ብለዋል።

የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ እና የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ግርማ ባሻ የክልሉን የጋራ ምክር ቤት አፈፃፀምን በዝርዝር አቅርበዋል ።

የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ና የዞኑ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መንገሻ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር ልማትና አንድነት የሚሰሩት ሥራ ሁሉን አቀፍ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል

አቶ መስፍን አክለውም የጋራ ሥራ ጠቁመው ፀጋንም ለመጠቀም ዘላቂ ሠላም መኖር ወሳኝ በመሆኑ የፓለቲካ ፓርቲዎች በጋራ መስራት አለባቸው ብለዋል።

በዞኑ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የተጠናከረ እንዲሆን የዞኑ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ከተሳታፊዎቹ የተለያዩ ጥያቄና አስተያየት ተነስቶ ውይይት ከተደረገበት በኃላ ዕቅድ አፈፃፀሙን ተቀብለው አፅድቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *