የአውሮፓ ሕብረት የተፈጥሮ ሀብት ላይ ጉዳት እየደረሰ የሚመረቱ ምርቶችን በተመለከተ ባወጣው ህግ ላይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ ውይይት ተደረገ

Spread the love

የውይይት መድረኩን ያዘጋጁት Consortium for Climate Change – Ethiopia እና NABU Ethiopia የተሰኙ ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች በመተባበር ነው።

በህጉ አተገባበር እና ተግዳሮቶች እንዲሁም ከአካባቢያዊ ሁኔታዎች አንፃር ግንዛቤ መፍጠር የመድረኩ ዓላማ ነው።

የNABU ኢትዮጵያ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አስተባባሪ አቶ አሳየ ዓለማየሁ በመድረኩ እንደተናገሩት ፤ ውይይቱ ባለድርሻ አካላት ይህንን ህግ ባከበረ መንገድ ማምረት እንዲችሉና ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ያደርጋል።

ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቡና ልማት ላይ የተመሠረተ ኑሮ የሚመራ ህዝብ ያለበት አካባቢ በመሆኑ በአዲሱ የአውሮፓ ህብረት ህግ ምክንያት እንዳይጎዳ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ ቡና፣ ሻይ እና ቅመማ-ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ በበኩላቸው ፤ አብዛኛውን የኢትዮጵያን እና የክልሉን ቡና የሚገዙት የአውሮፓ ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ከሚገኘው የቡና ሽፋን 65 በመቶው የሚሸፈነው በአርሶ-አደሮች በመሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው ከፍተኛ ርብርብ የሚፈልግ ነው ብለዋል።

በከፍተኛ አምራቾች እና በቡና አቅራቢዎች ስለወጣው ህግ፣ በትብብር ስለመስራት፣ ችግሮችን ስለመፍታት ውይይት የሚደረግበት መድረክ በመሆኑ ጠቀሜታው ጉልህ ነው ብለዋል።

በNABU ኢትዮጵያ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ማስተባበሪያ የገበያ ልማትና እሴት ሰንሰለት ባለሙያ የሆኑት አቶ ልሳኑ ተሾመ የውይይት ሰነድ አቅርበዋል።

በቀረበው ሰነድ ላይም የአውሮፓ ሕብረት ያወጣው ህግ ሰባት ዓይነት ምርቶችን የሚመለከት መሆኑን ጠቁመው ፤ ከእነኚህ ውስጥ ቡናና የከብት እርባታ ስራዎችን የሚመለከቱት መመሪያዎች በቀጥታ ኢትዮጵያን እና ክልሉን ይመለከታሉ ብለዋል።

ህብረቱ ያወጣው ህግ የአየር ንብረት እንዲለወጥ እና የዓለም ሙቀት እንዲጨምር በሚያደርግ ሁኔታ የሚመረቱ ምርቶችን ለማስቆም ነው።

በዚህም ከወጣው ህግ ጋር የሚጣጣም ምርት ለማቅረብ እንዲቻል የመረጃ አያያዝ ስርዓትን ማሻሻል፣ ስጋቶችን መለየት፣ ለተለዩ ስጋቶች መፍትሔ ማስቀመጥ፣ ምርቶች ደን ሳይጨፈጨፍ መመረታቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአውሮፓ ሕብረት ያወጣው ህግ በ27 የህብረቱ አባል ሀገራት የተፈረመ ሲሆን ፤ የከብት እርባታ እና የቡና፣ የካኮዋ፣ የዘይት ተክል፣ የሶያ ምርቶች እንዲሁም የፕላስቲክ እና የእንጨት ውጤቶች ደን ላይ ውድመት ሳያደርሱ የተመረቱ ከሆኑ ብቻ እንደሚገዛ ገልጿል።

በቀረበው ሰነድ ላይ ውይይት ተደርጎና ሀሳቦች ቀርበው ከመስምምነት ተደርሷል።

በመድረኩ በክልሉ የሚገኙ ቡና አምራቾችና አቅራቢዎች፣ በግልና በህብረት በቡና ልማት ዘርፍ የተሰማሩ አካላትና ከፍተኛ የመንግሰት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል ሲል ቦንጋ ኤፍኤም 97.4 ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *