የክልሉ ጸጥታ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በማካሄድ የተለያዩ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፥የፀጥታ ጋራ ምክር ቤት ጉባኤ በክልሉ ነባራዊ የፀጥታ ሁኔታዎችና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በሚዛን አማን ከተማ መክሯል።

በክልሉ የፀጥታ ችግር በነበረችው አከባቢዎች በተሰራው ጠንካራ ስራ አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ምክር ቤቱ ገምግሟል።

በክልሉ የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አርብቶአደር ቀጠናዎች በቅንጅት በተሰራው ውጤታማ ሥራ ተቋርጦ የነበረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ዳግም ማስቀጠል መቻሉ በምክር ቤቱ ተነስቷል።

በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት በምዕራብ ኦሞ ዞን፥ በሱሪ እና ቤሮ ወረዳዎች በእርስበርስ ግጭት የተቋረጠውን መንገድ ማስከፈት እና የጋራ ገበያ ዳግም ማስጀመር መቻሉን ምክር ቤቱ በአዎንታ ገምግሟል።

ክልሉ ድንበር በሚጋራበት የጎረቤት ደቡብ ሱዳን እንዲሁም ከአጎራባች ክልሎች ጋር ሠላማዊ ግኑኝነት መኖሩ የተገለጸ ሲሆን ይህንን ግኑኝነት በማጠናከር በቀጠናው ዘላቂ የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ማሳደግ እንደሚገባም ተመልክቷል።

በአርብቶአደር ቀጣና ውይይት በማጠናከር የእርስበርስ ግኑኝነት ከማደስ ባሻገር የህግ የበላይነትን በተገቢው የማረጋገጥና ተጠያቂነት የማስፈን ሥራ በመሰራቱ ከዚህ ቀደም በአባቢው ይስተዋል የነበረውን ግጭት መከላከል መቻሉ ተገልጿል።

ሰሞኑን በክልሉ በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ሾምባ ኪጪ ቀበሌ የአንድ ግለሰብ መገደልን ተከትሎ የተፈጠረዉን ክስተት ምክር ቤቱ በዝርዝር ገምግሟል።

በዚህም በአካባቢዉ ተፈጥሮ የነበረዉን ክስተት ህዝብ ጋር በመሆን ቁጥጥር ስር እንዲዉል መደረጉን፣በወንጀል የተጠረጠሩ አካላትን በህግ ቁጥጥር ስር እንዲዉል መደረጉን፣እንዲሁም በቀጣይም የህዘብ ለህዝብ ዉይይቶች ተካሂዶ* አካባቢዉ ወደ ሚታወቅበት ሠላማዊነት ሙሉ በሙሉ እንዲመለስ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ሠላም እንዳይመጣና ግጭት እንዲባባስ በማህበራዊ ሚዲያ ጭምር ግጭት የሚቀሰቅሱ የግጭት ጠማቂዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ምክር ቤቱ አስጠንቅቋል።

በክልሉ እየጨመረ የመጣው የጦር መሳሪያ ዝውውርና ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ትኩረት የሚሻ ተግባር መሆኑን የገመገመው ምክር ቤቱ በየደረጃው ያለው የፀጥታ መዋቅር የቁጥጥር ስረዓት ማሻሻል እንደሚገባ አስገንዝቧል።

በከተሞች የሚከሱ የወንጀል ተግባራትን የመከላከል ትኩረት የሚሻ መሆኑን የገመገመው ምክር ቤቱ በየደረጃው ያለው የፀጥታ መዋቅር ተቋማዊ አደረጃጀት በማጠናከር የወንጀል መከላከል ተግባር ማዘመን እንደሚገባም አስገንዝቧል።

የፀጥታ መዋቅር የህግ በላይነት ማስከበር ስራን በተጠያቂነት መንፈስ ማከናወን እንደሚጠበቅበት ያስገነዘበው ምክር ቤቱ በብልሹ አሰራር ውስጥ ተዘፍቀው ፍትህ የሚያዛቡ አካላትን የክልሉ መንግሥት ተከታትለው ለፍርድ እንደሚያቀርብም አስታውቋል።

በስተመጨረሻም በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች የጋራ ምክር ቤት አደረጃጀት መጠናከር እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *