ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ጉባዔ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆና ተመረጠች

Spread the love

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ጉባዔ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆና መመረጧን የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አስታወቀ።

ከጥቅምት 20 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በዚምባብዌ ቪክቶሪያ ፎልስ ከተማ በተካሄደው 7ኛው የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ጉባዔ ላይ ነው ኢትዮጵያ የኮሚቴው አባል ሆና የተመረጠችው።

ጉባኤው ”ሰብዓዊ ክብርን መሰረታዊ እሴትና መርህ ማድረግ የሕገ መንግሥት አተረጓጎም መነሻ እንዲሁም መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች እና ነፃነቶች ጥበቃና አፈፃፀም” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄዱም ታውቋል።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ወዬሳ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ በመድረኩ የነበራት ንቁ ተሳትፎ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆና እንድትመረጥ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሳትፎና ተደማጭነት ከማሳደግ ባለፈ ሕገ መንግስት ትርጉም ላይ የተሻለ አፈፃፀም ካላቸው ሀገሮች ልምድ እንድትቀስም ያስችላታል ብለዋል።

ጉባዔው ሀገራት በሕገ-መንግስታዊ ፍትህና በሕገ መንግስታዊ ዳኝነት ላይ ልምድ የሚለዋወጡበት መሆኑን በማንሳት።

ይህም የአፍሪካ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች በትብብር እንዲሰሩና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን እንዲያስከብሩ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ኮንፍረንስ ላይ ልምዷን እንድታካፍል መመረጧን ጠቁመዋል።

በኮንፍረንሱ የህገ-መንግስት ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ተቋማትና የጉባዔው አባል ሀገራት የህገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶችና ታዛቢ ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን እ.ኤ.አ በ2017 ነበር የተቀላቀለው።

የ48 የአፍሪካ ሀገራት ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት አባል ሲሆኑ ከአፍሪካ ውጪ ያሉ አራት ሀገራት ማለትም፣ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ቱርክና ኢራቅ ህገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች ደግሞ በታዛቢነት ይሳተፋሉ ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *