የክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በተጨባጭ እንዲረጋገጥ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀራረብ እየተሰራ ነው፦አቶ ነጋ አበራ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት ፋይናንስ ቢሮ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የ3ኛ ዙር የጋራ ምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ የክልሉ መንግስት ፈጣንና ቀልጣፋ የልማት ስራዎችን ለህዝቡ ተደራሽ ለማድረግ በርካታ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት እየሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህም የክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በተጨባጭ እንዲረጋገጥ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀራረብ እየተሰራ ነው ብለዋል አቶ ነጋ አበራ።

ብልፅግና ፓርቲ እየሰራ ያለው ሰው ተኮር ስራዎች ከግብ እንዲደርስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተግባር እንዲጠናከርና ሎሎችም ድርጅቶች ወደ ክልሉ መጥተው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድህነትን ከመቀነስ ባለፈ ነጻና ገለልተና በመሆን ለጠንካራ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያላቸው አስተዋጽኦ ጉልህ እንደሆነም ተናግረዋል።

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ እንደገለጹት፤ በክልሉ ያለው እምቅ አቅሞችን ወደ ተጨባጭ ሀብት ለመቀየርና የህዝቦችን አንገብጋቢና መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎችን ባልተራዘመ ጊዜ ደረጃ በደረጃ እየመለሰ መሄድ እንዲቻል ትኩረት ተሰጥቷል።

በክልሉ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጤና ዘርፍ ፤በግብርና፤በትምህርት፤በውሃ ልማት፤በአከባቢ ጥበቃ፤ በሴቶችና ህጻናት መብቶችና መሰል ዘርፎች እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እነዚህም ድርጅቶች ከ4.3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በመያዝ በየዓመቱ በአማካይ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማፍሰስ በሁሉም ዞኖች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸው የልማት ስራዎችን እየሰሩ ነው ብለዋል።

አሁንም በክልላችን ካለን የመልማት አቅምና ካለው የልማት ክፍተት አንጻር አሁንም በርካታ ስራ ይጠይቃል ያሉት ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች መደገፍና የሚያጋጥማቸው ችግሮችን በመፍታት ረገድ በትኩረት እየተሰራ ነው መሆኑንም ተናግረዋል።

ክልሉ አስተማማኝ ሰላም ያለው የተረጋጋ፤መልካም የስራ ባህልና በተፈጥሮ ሀብት ያለበት ክልል በመሆኑ ድርጅቶች በክልሉ መጥተው በልማት ስራ እንዲሰማሩ ምቹ አጋጣሚዎች እንዳሉትም አክለው ገልጸዋል ኃላፊዋ።

በመድረኩ በክልሉ በተለያዩ ዞኖች እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የስራ ረፖርት እየቀረበ ይገኛል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *