


የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን፣ በምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ጀሙ ከተማ ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ ለሚገነባው የፓርቲ ቅርጫፍ ጽ/ቤት ህንጻ የመሠረተ ድንጋይ አኑረዋል።
በመርሐግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፥ ባለፋት የለውጥ ዓመታት በብልፅግና ፓርቲ መሪነት እንደሀገር እንዲሁም በክልል ደረጃም በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።
የተገኙ ድሎች ቀጣይነት በማረጋገጥ የዜጎችን ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል የተቋም ግንባታ ወሳኝ ነው ያሉት ኃላፊው፥ ግንባታው ተጀምሮ እስከ ጠናቀቅ የአባላትንና ደጋፊዎች ተሳትፎ መጠናከር አለበት ብለዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን በበርካታ የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ሀብቶች የበለፀ መኾኑን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፤ ይህንንም ፀጋ ወደ ሚጨበጥ ሀብት በመቀየር የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የአመራር ስርዓት መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የአከባቢን ሠላም ማስጠበቅ ለአንድ ወገን የሚተው ተግባር አለመኾኑን የገለጹት አቶ ፍቅሬ፥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለሠላምና ደህነት መጠበቅ የአከባቢው ማኅበረሰብ ተግተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የህዘብ የልማት አቅም በማቀናጀት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መፍታት መቻሉን የጠቆሙት አቶ ፍቅሬ፥ በቀጣይም ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የባለ ሶስት ወለል የፓርቲ ህንፃ ግንባታው ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ በጀት እንደሚገባ የገለጹት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታምሩ ቦኒ፥ የአባላትንና ደጋፊዎች ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በመርሐግብሩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ፣ የክልሉ ረዳት የመንግሥት ተጠሪዎችን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች እና የአከባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
