ለመንገድና ድልድይ ግንባታ የዲዛይን ስራዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የፕሮጀክት ውጤታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተመላከተ።

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ የመንገዶች ባለስልጣን መስሪያ ቤት፥በክልሉ በአማካሪ ድርጅቶች የተሰሩ የመንገድ እና የድልድይ ፕሮጀክቶች ጥናትና ዲዛይን ሥራ ሪፖርት በቦንጋ ከተማ ግምግሟል።

በዲዛይን ግምገማው መድረክ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አብድዩ መኮንን ለመንገድና ድልድይ ግንባታ የዲዛይን ስራዎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት የፕሮጀክት ውጤታማነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአንድን ፕሮጀክት ግንባታ ውጤታማነት ለማረጋገጥ የጥናትና ዲዛይን ተግባር የጎላ ድርሻ እንዳለው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ የጊዜና የሀብት ብክነት በመቀነስ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቁ ለማስቻል ለጥናትና ዲዛይን ተግባር ትኩረት ልሰጥ ይገባል ብለዋል።

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ስር በሚገኙ ዲስትርክቶች በርካታ የመንገድና የድልድይ ግንባታ ስራዎች በበጀት ዓመቱ በነቃ የህብረተሰብ ተሳትፎ መከናወናቸውን የገለጹት እንጂነር አብድዩ፥ ይሁን እንጂ በክልሉ ሰፊ የመሠረተ ልማት ክፍተት ያለበት በመሆኑ የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት በተገቢው ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሀብት ውስንነት፣ የሚሽነሪ ጥገናና የግንባታ ግብዓት እጥረት ለዘርፉ ውጤታማነት ማነቆ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ የህብረሰቡን የልማት አቅም በማቀናጀት የክልሉን አቅም ታሳቢ ያደረገ የልማት ተደራሽነት ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ውጤታማ የጥናትና ዲዛይን ጊዜና ገንዘብ ከመቆጠብ ባሻገር በግንባታ ወቅት ልያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በመቅረፍ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የግንባታ ጊዜ ተጠናቀው ለአግልግሎት እንበቁ እንደሚያደርግ የገለጹት የመድረኩ ተሳታፊዎች ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በክልሉ በተለዩ 15 የመንገድ እና 12 የድልድይ ፕሮጀክቶች ላይ በአማካሪ ድርጅቶች የተሰሩ የጥናትና ዲዛይን ስራዎች ሪፖርት ቀርቦ ተገምግሟል።

በመድረኩ አማካሪ ድርጅቶች፣ የክልሉ የገጠር መንገድ የዲስትርክት ስራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *