ቆይታ ከእኛ ጋር!

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተፈጥሮ ጸጋዎች የበለጸገ፤ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሀ ባለቤት፤ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ እጅግ ጥቅጠቅ ያሉ የተፈጥሮ ደኖች ያሉበት፤ ወንዞች፣ ፏፏቴዎች፣ ሐይቆች፣ ብርቅዬ እንስሳትና አዕዋፋት እንዲሁም በርካታ የተፈጥሮ ስጦታዎች ያሉበት ክልል ነው፡፡

ክልሉ ከሚታወቅባቸው የከርሰ ምድር ጸጋዎች መካከል የድንጋይ ከሰል፣ የወርቅ ማዕድን፣የኮንስትራክሽን ማዕድናት፣ የብረት ማዕድናትና ሌሎች ጸጋዎች በስፋት የሚገኙበት ድንቅ ምድር ነው፡፡

በዚህ ዝግጅታችን የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ከክልሉ ማዕድን ኤጀንሲ ጋር በክልሉ እየተከናወኑ ስለሚገኙ ማዕድናትን የማውጣትና የማስተዳደር የስራ እንቅስቃሴን የተመለከተ ቆይታ አድርገናል መልካም ንባብ፡፡

መ/ኮ ፡-በቅድሚያ ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

መ/ኮ ስምና ኃላፊነትዎን ቢገልጹልኝ

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ፡- ስሜ አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ እባላለሁ የክልሉ ማዕድን ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር

መ/ኮ ፡-ከክልሉ ምስረታ ወዲህ ባለፉት ሶስት ዓመታት የማዕድን ጸጋዎችን ለይቶ ከማልማት አንጻር እየተሰራ ያለ ስራ ምን ይመስላል?

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የማዕድን ፖቴንሻል ሲሰራ የማዕድኑ ክምችት ያለበት ቦታ  በመደረስ  የማዕድኑ አይነት የማዕድኑ ይዘትና መጠን ፤ምን ያክል ክምችት እንዳለው መረጃ ይሰበሰባል ፣ በቦታው በመገኘት ዳሰሳ ይደረጋል ፡፡ ይህ የማዕድን አለኝታ ወይም ፖቴንሻል ስራ ሲሰራ በዘርፉ ባለሙያዎች (ጂኦሎጂስቶች) ክምችቱ ባለበት ቦታ ለፖቴንሻል ጥናት ወሳኝ መረጃዎችን ይሰበሰባሉ፡፡

የማዕድን ክምችቱን ለማጠናት የሚከተሉ መረጃዎች ይሰበሰባሉ፡፡

  • ፖቴንሻሉ የሚገኝበት ጂፒኤስ  እና ማዕድኑ የሚገኝበት ዞን ወረዳ ቀበሌ የአካባቢው ልዩ መጠሪያ ስም ያከተተ መረጃ ይሰበሰባል፡፡
  • ናሙና ይሰብሰባል
  • የተሰበሰበው ናሙና ላብ አናሊስስ ይስራል (lab analysis)
  • የተሰበሰበው ናሙና  ወጤት ይተነተናል (interpretation)  

የመስክ ዳሰሳ መረጃ፤ ላብራቶሪ ወጤት እና የቢሮ ስራ ጋር በማቀናጀት  የማዕድኑን የኢኮኖሚክ ቫልዩ (Economic value)፤ማርኬቱን ጥናት ከተደረገ በኃላ  ሰነድ በማዘጋጀት  ለአካባቢ ማህበረሰብ የስራ ዕድል እንዲፈጠር ማደረግ፤ በማዕድን ዘርፍ ለሚሰማሩ በለሀብቶች/ኢነቨሰተሮች /ባለድርጀቶች  በዚህ ማዕድን ዘርፍ እንዲያለሙ ጭምር በአካባቢ ላይ ለስራ አጡ ዜጎች የስራ ዕድል እዲፈጠር ምቹ ሁኔታዎች መፍጠር፤በተጨማሪም ባለሀብቱ/ኢነቨሰተሩ  እንደ ማዕድኑ አይነትና ይዘት ሀገሩን፣ ማህበረሰቡን እና እራሱን  እንዲጠቅም ይደረጋል፡፡ በማዕድን   የአዋጭነት ሰነድ በማዘጋጀት   አዋጭ በሆነ መልኩ መሰራት እንደሚችል የሚያሳይ የጥናት ሰነድ እዲቀርብ ተደርጎ ከአካባቢ ማህበረሰብ ጋር ተጽኖ በማያመጣ መልኩ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ከባለደርሻ አካላት ጋር በመሆን መንግስትና ህዝብ ከባለፍቃዱ ማግኘት ያለበትን ገቢ በመከታተል የክልሉ መንግስት ገቢ እንዲጎለብት የማድረግ ስራዎች ይሰራሉ፡፡  

 መ/ኮ፡-  በክልሉ አሉ ተብለው የተለዩ የማዕድን አለኝታዎች ምን ምን ድናቸው? በየትኛው የክልሉ አካባቢዎች ይገኛሉ?

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ፡-  በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የማዕድን ፖቴንሻሎች (ጸፀጋዎች) በተመለከተም

  1.  ኮንስትራክሽንና ኢንዱሰትሪ ማዕድናት
  2. እምነበረድ ኮንስትራክሽንና ኢንዱሰትሪ ማዕድን (ም/ኦሞና ሸካ ዞን ይገኛሉ)
  3. ግራናይት  ኮንስትራክሽንና ኢንዱሰትሪ ማዕድን (ቤንች ሸኮ፣ ሸካ ዞን ፣ዳዉሮ ዞንና ም/ኦሞ ዞን በሰፊው ይገኛል)
  4. ድንጋይ ከሰል በስድሰቱም ዞን ይገኛል
  5. ከኦሊን ኢ/ማዕ  (ዳዉሮ፣ ኮንታና ቤንች ሸኮ ዞን ይገኛል)
  6. ላይምሰቶን (ዳዉሮና ኮንታ ዞን ይገኛል)
  7. ላይም በስድሰቱ ዞን ይገኛል
  8.  ጄም ስቶን( የተለያዩ ጄም ስቶንስ (6ቱም ዞን ላይ ይገኛል)

3.  የከበረ ማዕድን እና በከፊል የከበረ ማዕድን በስድሰቱ ዞን ይገኛል

4. ብረትና ብረት ነክ (ካፋ፣ዳዉሮ፣ኮንታ፣ ቤንች ሸኮ ዞንና ም/ኦሞ ዞን ይገኛል)

 መ/ኮ ፡-   የወርቅ ምርተ በየዓመቱ አፈጻጻሙ እንዴት ይገለጻል ?

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ ፡-  በፌደራል፣ በክልል፣ በዞንና በወረዳ የኤክስፖርት ማዕድን ምርት ግበረኃይል ተቋቋሞና  ከተለያዩ ባድርሻ አካላት ጋር በመሆን የኤክስፖርት ማዕድን የግብይት ሰንሰለት (ከምርት አንሰቶ እስከ ብሄራዊ ባንክ) ያለውን ዉስንነት በመከታተል ወጥ የሆነ ድጋፍና ቁጥጥር ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

አፈጻጸሙን በተመለከተ በ2014ዓ.ም 250ኪ.ግ፣ 2015ዓ.ም 67ኪ.ግ፣ 2016ዓ.ም 90.5 ኪ.ግ ና 2017 ዓ.ም እከዚህ ሩብ ዓመት 50ኪ.ግ ነዉ፡፡ ዝቅተኛ አፈጻጸም ቢመዘገብም  በ2017ዓ.ም እንደ ሀገር  በተደረገው ማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ወዲህ  የተሸለ አፈጻጸም እየተመዘገበ ይገኛል፡፡ መንግስት እንደ ሀገር ያደረገው  ማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የኤክስፖርት ማዕድን ጥቁር ገብያን እየቀነሰ መሆኑን እንደ ክልልም ሆነ እነደ ሀገር የኤክስፖርት ማዕድን  አፈጻጸም ሪፖርት መጨመሩን ያሳያል፡፡ ስለዚህ የተደረገው ማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ኤክስፖርት ማዕድን ዘርፉ ላይ አዎንታዊ ተጽኖ አምጥቷል ማለት ይቻላል፡፡

መ/ኮ ፡-   አሁን በመልማት ላይ የሚገኙ ማዕድናትን ለአብነት ሊጠቅሱልኝ ይችላሉ?

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ፡- በዋናነት በክልሉ በመልማት ላይ የሚገኙ የማዕድን ፀጋዎች የሚከተሉት ናቸው

  • የኤክስፖርት ማዕድን (ወርቅ ም/ኦሞ ዞን)
  • ዲንጋይ ከሰል (ደውሮና ኮንታ)
  • ኮንስትራክሽን ማዕድን (6ቱ ዞን )

 በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ማዕድን በመልማት ላይ ያሉና እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አካባቢ ህበረተሰብ ስራ ዕድል በመፈጠሩ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዝ ዘርፍ ነው፡፡ በ2016 በማዕድን ዘርፉ በክልሉ ወደ 5323 የሚሆኑ የክልሉ ዜጎች የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡

መ/ኮ ፡-  የወርቅ ማዕድን አመራረት ሂደቱ እንዴት ይገለጻል ቢያብራሩ። ከዘመናዊነትና ከባህላዊ የአመራረት አኳያ ቢለይ

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ ፡- የአሰራር ዘይቤውን በተመለከተ ቀደም ሲል የቤሮ ወረዳ ወርቅ የአመራረት ዘይበው በባህላዊ አመራራት ዘዴ ሲሆን በአካባቢው በቀበሌው ነዋሪዎች በማህበር በመደራጀት ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ  የደለል ወርቅ ክምችት ያለበት በማህበር በመሆን ቀለል ባሉ የማዕድን ማምረቻ ዶማ፤ አካፋ፤ ዲጂኖ፤ ሽብልቅ ፤ የወርቅ ማጠቢያ ገበቴ በመጠቀም የሚመረት ባህላዊ ወርቅ የማምረት ዘዴ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባህላዊ ወርቅ አምራች ማህበራት በመቀነስ አምራች ሀይል ወደ ዘመናዊ አመራረት ፍላጎት በማሳየት በዘመናዊ አመራረት ዘዴ በልዩ አነስተኛ የደለል ወርቅ ምርት በመሳተፍ ፊት ከነበረው 16 ወደ 56 ልዩ አነስተኛ ወርቅ አምራች ተደራጅተው ህጋዊ የማምረት ፍቃድ ወስደው ውደ ስራ ገብተዋል፡፡ ይህ ዘመናዊ ወርቅ የማምርት ዘዴ እንደ ባህላዊ በትንሽ ወጪ የሚሰራ አይደለም፡፡ በዘመናዊ ወርቅ አመራረት ዘዴ ሲሰራ በተጠና መልኩ እና በዋናነት ማሽነሪዎችን በመጠቀም  በትንሽ የሰው ኃይል የሚሰራ የአመራረት ዘዴ ነው፡፡ አሁን ባለበት ደረጃ ካሉት የወርቅ ምርት ፍቃዶች ውስጥ 60 ፍቃዶች ውስጥ 93.10% የሚይዘው ዘመናዊ ወርቅ የማምረት ዘዴ ነው፡፡ በዘመናዊ መንገድ ወርቅ ሲመረት ሊጠቀማቸው ከሚችሉ ከባድ ማሽነሪዎች (እስካቫተር ፤ ሎደር፤ ማጠቢያ ማሽንና ውሃ ፓምፕ የመሳሰሉትን በመጠቀም የለይኛውን አፈር ማንሳት ስራ፤ ወርቅ አዘሉን አፈርና ድንጋይ መለየት፣ መቆፈር፣ መሰብሰብ በመጨረሻም ወርቅ ያዘለውን አፈር በወርቅ ማጠቢያ ማጠብና ማጣራት ስራ ይሰራል፡፡ በዚህም መንገድ የመጨረሻው Gold Recovery Method ወርቅ የማጣራት መንገዱ በገበቴ ሲሆን አሁንም ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ ነው ብሎ ለማዉራት አይቻልም ምክኒያቱም 40-50% በገበቴ ሲታጠብ እና የአስተጣጠብ ዘዴው አሁንም ከብክነት የነጻ አይደለም፡፡ ከፈደራል እና ከክልሎች የተወጣጣ የባለሙያ ቡድን (value Chain Analysis)  ዳሰሳ ጥናት በቤሮ ወርዳ ልዩ አነስተኛ አምራች ማህበራት ላይ ስለ አሰራሩ መረጃ በመሰብስብ ከ2 ወር በላይ የጥናት ቡድን ወርክሾፒ በመቆየት ከምርት አነስቶ እስከ ባንክ ድረስ ያለውን የግብይትና የምርት ሰንሰለት ያለውን ውስንነት በጥናት በመደገፍ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በማስቀመጥ የአመራረት ዘዴው መሻሻል ያለበት ስለሆነ ምርት ለማሻሻል የሚያስፈልጉትን አማራጮች በቴክኒና ሙያ ቢሰሩ ወይም  ቴክኖሎጂው ሽግግር  ተደርጎ ቢመጣ ብክነት የሚቀንስ መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል፡፡

መ/ኮ፡-  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወርቅ ማዕድን በህገ-ወጥ መንገድ እየተመረተ አፈጻጸሙ ዝቅ እያለ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህ ዋነኛ ችግር ምንድነው ቢገልጹልን?

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ፡-ወርቅ በተፈጥሮ ባህሪው ለጥቁር ገብያ ምቹ በመሆኑ በባህሪውም የማይበሰብስ፤ የማይዝግ ስለሆነ በተለያየ መንገድ በህገ ወጥ ሊዘዋወር መንግስትም ከዘርፉ የምርቱን ያክል ማግኘት ያለበትን የውጨ ምንዛሬ እያገኘ አይደለም ፡፡ለዚህ ዋነኛ ችግር ተብለው የሚጠቀሱ

  • ወጥ የሆነ ድጋፍና ቁጥጥር አለመኖሩ
  •  የመሰረት ልማት ተደራሽነት ያለመሆን፣
  • ህገ ወጥ የወርቅ ግብይትና ዝውውር፣ መበራከት
  • ስራውን በእየጊዜው ወርዶ ዝርዝር ተግባሩን  ለመደገፍና ቁጥጥር ለማደረግ የበጀት ውስንነት እና የምርት ዜይቤዉ ዘመናዊ ያለመሆን ለአፈፃፀም ማነስ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
  • በቂ በጀት አለመመደብና፤ከስራው ስፈትና ትኩረት አኳያ በቂ ተሸከርካሪ አለመመደቡ፤ የባለሙያ እጥረት በዚህም ምክኒያት በእየጊዘው ድጋፍና ቁጥጥር አለማደረግ ችግሮች ተብሎ የተለዩ ናቸዉ፡፡

መ/ኮ፡-  አሁን ላይ ህገ-ወጥነትን በመከላከል ህጋዊነትን በማስፈን ምን እየተሰራ ይገኛል

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ፡- ይህ ኤክስፖርት ማዕድን የሀገር የኢኮኖሚ ዋልታ መሆኑ የሚታውቅ ነው፡፡ ምክኒያቱም ሀገራችን የውጭ ምንዛሪ የምታገኘው ከዚሁ ዘርፍ ስሆን እንደ ክልል ይህን ህገ-ወጥነት ለመከላከል በጋራ  ከፌደራል አንስቶ እስከ ወረዳ በመቀናጀት ከምርት አንስቶ እስከ ባንክ ያለውን ስንሰለት የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ባሁኑ  ጊዜ የኦፕሬሽንና ቁጥጥር  ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡ ምርት በሚመረትባቸው ቀበሌዎች መውጫና መግቢዎች ላይ ህገ-ወጥ የማዕድን ዝውውርና ግብይት እንዳይኖር ኬላ(ጥበቃ) የማዘጋጀት ስራዎች እየተሰሩና የአፈፃፀም ለዉጥ እየታየ ይገኛል፡፡

መ/ኮ ፡-ህገ-ወጥነትን ከመከላከል አኳያ የባለድርሻ አካላት ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ?

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ ፡- ይህንን የኤክስፖር ማዕድን ህገ-ወጥነትን ለመከላከል በመላው የመንግስት መዋቅርና በተቋቋመው የኤክስፖረት ማዕድን ግብረ-ኃይል ከፌደራል አንስቶ እስከ ታችኛው መዋቅር ጋር በመቀነጀት ከምርት አንስቶ እስከ ግብይት ደረስ ያለውን ሰንሰለት በመከታተል የድጋፍና ክትትል ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ለባለፍቃዶች የምርት ዕቅድ እንዲያቅዱ ተደርጎ አፈጻጸማቸውን በመገምገም በማዕድን ደንብና መምሪያ መሰረት ምርት በሚሰውሩ ባለፍቃዶች ላይ ኤጀንሲው የዲሲፕሊን እርምጃ እየወሰደና እያስተማረ ይገኛል፡፡

መ/ኮ ፡-  በቀጣይስ ይህንን አጠናክሮ ከማስቀጠል አኳያ የተያዘ ዕቅድ ካለ?

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ፡- በቀጣይ በኤጀንሲው የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት

  • ከክልሉ ጀምሮ አስከ ታችኛው የወረዳና የቀበሌ ባለድርሻ አካላት ጋር በተግባሩ ዙርያ ውይይት ማድረግና አቅጣጫ መስጠት
  • የንቅናቄ መድረክ በምዕራብ ኦሞ ዞን ጀሙ ከተማ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በክልሉ ከፍተኛ አመራር ይመራል፡፡
  • በወርቅ ምርትና ግብይት እንዲሁም ዝውውር የተሰማሩ ባህላዊ አምራች ማህበራት፣ ግብይት ማህበራት፣ ልዩ አነስተኛና በግል አቅራቢነት ፍቃድ የወሰዱ አካላትን መለየት፤
  • የወርቅ ምርትና ግብይት እንዲሁም የማቅረብ ፍቃድ ወሰደው ወደ ስራ ያልገቡትን በመለየት ወደ ተግባር ገብቶ ውጤት ማምጣት የሚችሉት ወደ ህጋዊነት ማስገባትና ወደ ተግባር የማይገቡትን ፍቃዳቸውን መሰረዝ
  • በህጋዊ መንገድ የወርቅ ምርትና ግብይት እንዲሁም ዝውውር የሚካሄድበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር
  • የወርቅ ምርትና ግብይት ስርዓት በመረጃ ተደግፎ በየዕለቱ የሚዘገብበት ስርዓት መዘርጋቱን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ማረጋገጥ፣
  • ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ የሚያቀርብ ባለፍቃድ በትክክል ወደ ባንክ እያቀረበ መሆኑ በመረጃ ምዝገባ ስርዓት እተከናወነ መሆኑን ማረጋገጥና አሰራር መትከል 
  • የወርቅ ማዕድን ከህግ ውጪ የሚያመርቱ፣ የሚያከማቹ፣ በህገ-ወጥ መንገድ የሚያዘዋውሩ፣ በጥቁር ገበያ የሚገበያዩ፣ የሚደልል ህገ-ወጥ አካላትን መለየትና እርምጃ መውሰድ
  • በተመረጡና በተለዩ ቦታዎች የወርቅ ግብይት ማዕከል ማደራጀት
  • በአቅራቢያ ከሚገኙ የንግድ ባንኮች ጋር በወርቅ ምርት የተሰማሩትን አካላት ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግ
  •  በየዕለቱ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት እንዲኖር ማድረግ
  • ወርቅ በህገ ወጥ መንገድ የሚገዙ አካላት ላይ ድንገተኛ ፍተሻ ማደረግ
  • የተለያዩ ኬላዎች እንዲጠናከሩ ገምግሞ አቅጣጫ ማስቀመጥ፡፡

መ/ኮ፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ በክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ስም አመሰግናለሁ

አቶ ገብረማሪያም ሰጠኝ፡- እኔም ከልብ አመሰግናለሁ ፡፡

 በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *