የኮሪደር ልማት ስራን የተረዱትና የተገበሩት ሞዴል አርሶ አደር አቶ አመነ አምበሎ!

Spread the love

በሸካ ዞን ማሻ ወረዳ የካንጋ ቀበሌ ሞዴል አርሶ-አደር አቶ አመነ አምበሎ ቤታቸውን እና ግቢያቸውን ውብ፣ ጽዱና ለመኖር ምቹ ማድረግ ከአባቶች የወረሱት ባህል ቢሆንም ፤ አሁን መንግስት በሰጠው ትኩረት ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የቀለም ትምህርትን እስከ ሰባተኛ ክፍል እንደተማሩ የሚናገሩት ሞዴል አርሶ-አደሩ ፤ ስድስት ልጆችን በማስተማር ለውጤት ማብቃታቸውን ተናግረዋል።

ባላቸው ዕውቀትና ትጋት ጽዱና ምቹ አካባቢን ከመፍጠር በላይ በግቢያቸው ዙሪያ እንሰት፣ ጎመንና ፍራፍሬ በማምረት የተትረፈረፈ ማዕድ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ለስራቸው ስኬት የቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ ፤ መንግስት ለዚህ ስራ ለሰጠው ትኩረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ለሌሎች አርሶ-አደሮችም ተሞክሯቸውን በማካፈል ውብ አካባቢ እንዲፈጠር በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በሁለ-ገብ ተግባራቸውና በታታሪነታቸው የሚታወቁት አርሶ-አደር አመነ አምበሎ አዳዲስ ስራዎችን ለአካባቢው ከማሳየት አልፈው ፤ የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ ቀድመው በመረዳት ተግባራዊ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጎረቤቶቻቸው መስክረዋል።

ሞዴል አርሶ-አደር ስለመሆናቸው ምስክርነት የሰጡት ጎረቤታቸውና የቀበሌው አስተዳዳሪ አቶ አየለ አዴሞ ልምዳቸውን ለሌሎች በማጋራት አብሮ ማደግና መለወጥን የሚሹ ጠንካራ ሰው መሆናቸውን ገልጸዋል ሲል የማሻ ኤፍ ኤም 103.8 ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *