





ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ በተገኙበት ”ሀገራዊ የንግድ ሳምንት አከባበር አስመልክቶ የንግድና ኢንቨስትመንት ሴክተር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምስረታ ጀምሮ የእስካሁኑ ጉዞ እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ዓላማ ያደረገ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሂዷል።
በምክክር መድረኩ በንግድ እና እንቨስትመንት ዘርፍ እስካሁን ተከናወነዉ የተመዘገቡ ውጤቶችን ማጠናከር እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ማረም በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ምክክር ተደርጓል።
በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂገር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በብዛትና በጥራት በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካትና የውጭ ምንዛሬን ከማሳደግ ባለፈ ገበያን ለማረጋጋት በትኩረት መሥራት ይጠበቅብናል።
የንግድ ግብይት ሰንሰለትን ጤናማ ማድረግ፣ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን መቆጣጠር፣ የሰንበት ገበያን ማስፋፋትና ማጠናከር፣ በፍጆታ ምርቶች የሚስተዋሉ ህገወጥ ዝውውርና ኮንትሮባንድ ንግድን መከላከል፣የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ምርቶችን መቆጣጠርና ማስወገድ ይጠበቃልም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
እየጨመረ የመጣውን የከተማና የገጠር ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲጨምር አስፈላጊ ጉዳዮችን ማመቻቸት እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት፣ለአዳዲስ ኢንቨስትመንት ፍላጎት ምላሽ መስጠት፣ወደሥራ የገቡትን መቆጣጠርና ማበረታታት እንዲሁም በኢንቨስትመንት ሥም መሬት ወስደው ከማያለሙት መሬት ማስመለስና ወደመሬት ባንክ ማስገባት ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ማከልም በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተቀመጡ ስትራቴጅዎችን በፍጥነት በመፈጸም አምራቹና ሸማቹን ቀጥታ በማገናኘት ገበያን ለማረጋጋትና ኑሮ ውድነት ለመቀነስ ትኩረት ተደርገው እንዲሰራ አሳስበዋል።
በክልሉ ገበያን ማረጋጋትና ኑሮ ውድነት መቀነስ እንዲያስችል አምራቹን እና ከሸማቹ ጋር ቀጥታ ማገናኘት የሚያስችል የንግዱ ሰንሰለት መፍጠርና የሰንበት ገበያ እንዲስፋፋ መደገፍና ማጠናከር ሥራዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግም የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ ገልጸዋል።
የነዳጅ ሥርጭትና አስተዳደር የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በየደረጃው የተደራጀ ግብረሃይል በማጠናከር ይሰራል ያሉት የቢሮ ኃላፊዉ፤ የቦሎ ህትመት፣የንግድ ፍቃድ ምዝገባና እድሳት ዘመናዊ ማድረግ እንዲሁም የከተማና የገጠር ኢንቨስትመንት ዘርፍ በማጠናከር የኦኮኖሚ ዕድገት ለማሳደግ ትኩረት እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።
በፍቅር ከበደ
