‹‹‹‹‹‹ ሪፖርታዥ ››››››

Spread the love

ማህበራዊ ሚዲያን የህዝብን አንድነት በሚያጠናክር እና ሀገርን ማሻገር በሚያስችሉ በጋራ ጉዳዮች ላይ አትኩሮ መጠቀም ያስፈልጋል።

የድህረ እውነት ዘመንን ለመሻገር በተለያዩ የማህበራዊና ሜንስትሪም ሚዲያው ላይ የሚሰራጩትን ፀረ-ፓርቲ፣ ፀረ- መንግስትና በሀገራዊ ጥቅም ላይ የተቃጡ ስም ማጥፋት ዘመቻዎችን ለመመከት በእውቀትና በክህሎት መመራት ያስፈልጋል።

ሀሰተኛ ዘመቻዎችን በሁሉም መስክ ለመመከት የሚያስችል የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክህሎት መታጠቅና እውቀት መር የሆነና እውነትን መሰረት ያደረገ ምላሽ መስጠት የሚገባ በመሆኑ ዘመኑን የዋጀ ቁመና ላይ መገኘት አስፈላጊም ነው።

”የድህረ እውነት ዘመን በእውቀት እና በእውነት” በሚል መሪ ቃል ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አመራሮች፣ለኮሙኒከሽንና ሚዳያ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ባለፈው ሳምንት በቦንጋ ከተማ መሰጠቱ የሚታወስ ነው።

ስልጠናው የፓርቲ አመራሮችና የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች በድህረ እዉነት ዘመን ዉስጥ እንዴት ተቀናጅተው በእዉነት እና እዉቀት የሀገራችን እና የህዝቦችን ሃቅ በሚገባ እያስተዋወቀ የህዝቦችን አንድነት የሚንዱ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ እና ትክክለኛ መረጃዎችን በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው።

የፓርቲ አመራርና የኮሙኒኬሽን እና የሚዲያ ባለሙያዎች አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ የፓርቲውን ዓላማ እና እሳቤ በአንድነት በማጣመር በእውቀት እና በእውነት መምራት እንዲያስችል የተሰጠው ስልጠናው የጎላ ሚና እንዳለው በኮንታ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ በሻ በላቸው ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ወደ ሥልጠና ከመጣ ወዲህ የክልሉ ህዝቦች የረዥም ዘመን በክልል የመደራጀት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ የህዝቡን ሁሉዓቀፍ ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ የሚችሉ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች እየተሰራ ይገኛል።

እንደ አቶ ባሻ በላቸው ገለጻ፤ በፓርቲው እና በመንግሥት የሚሰሩ ሥራዎችን ለህዝቡ ለማሳወቅ ኮሙኒኬሽን እና ሚዲያ ትልቅ አቅም ያለዉ ዘርፍ በመሆኑ ዘርፉን በእውነት እና በእውቀት መምራት ያስፈልጋልም ብለዋል።

የሚሰሩ ሥራዎችን በተቃራኒው ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አካላትን መከላከል እና ለህዝቡ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት ከሰልጠናው ባገኘነው እውቀት በርካታ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል አቶ ባሻ በላቸው።

በየደረጃው ከማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ጉድሌቶችን ማረምና የማህበራዊ ሚዲያ ሠራዊትን በማደራጀት እና በመጠቀም አዎንታዊ መረጃዎችን ለህዝቡ ለማድረስ ከስልጠናው የተጨበጠውን እውቀት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።

አጠቃላይ የፓርቲ አመራርና አባላት ያለንበት የድጂታል ዘመን ተከትሎ የሚሰራጩ መረጃዎችን እውነትን እና ትክክለኛውን ለይቶ እና አጣርቶ መጠቀምና በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ መታገል ያስፈልጋል ሲሉም አቶ ባሻ ሀሳባቸውን ሰጥቷል።

የሸካ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ እና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘርሁን አንደም በበኩላቸው፣ የድህረ እውነት ዘመንን በእውነት እና በእውቀት በሚል መሪ ቃል ለክልል አመራሮች እና ለኮሙኒኬሽን እና ለሚዲያ ባለሙያዎች የተሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና የድህረ እውነት ዘመን በውል በመረዳት ወቅቱን የሚመጥን እውነተኛ እና ትክክለኛ መረጃ አጣርቶ እውነትን ከውሸት ለይቶ መጠቀም የሚያስችል አውድ ፈጥሯልም ብለዋል።

በአመራሩ እና አባሉ ዘንድ በመሠረታዊነት የሚስተዋለው በመረጃ ያለመቀናጀትና በአንድነት ያለመታገል እንዲሁም በሚዲያ አጠቃቀም የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ለመቅረፍ ስልጠናው ወሳኝነት እንዳለዉ ነው አቶ ዘርሁን አንደሞ የገለጹት።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በገዥው ፓርቲና በመንግሥት በየደረጃው የሚከናወኑ የተሻለ አፈጻጸሞችን ማስተዋወቅ እና የፓርቲውን እሳቤ፣ዓላማና ፕሮግራሞችን ለማስረጽ ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ አላማ ማዋል ይጠበቃልም ብለዋል።

አሁን ያለንበት የድጅታል እና ተለዋዋጭ ዘመን በውል በመረዳት የመረጃ በላይነት መያዝና የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ አካላትን በተገቢው መመከት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ፓርቲው በየጊዜው የአመራሩ እና የአባሉን የመፈጸም እና የማስፈፀም አቅም ለማጎልበት እንዲሁም የሚስተዋሉ የአመለካከት እና የሥነምግባር ጉድሌቶችን ለማስተካከል የጀመራቸው የአቅም ግንባታ ሥራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የካፋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ እና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታከለ ታምሩ ናቸው።

በድህረ እውነት ዘመን በእውነት እና እውቀት በሚል መሪ ቃል የተሰጠው የአቅም ግንባታ ሥልጠና ወቅቱን የሚመጥን ነው ያሉት አቶ ታከለ ታምሩ እውነተኛ መረጃዎችን ከሀሰተኛ መረጃዎችን በበቂ እውቀት፣ ክህሎትና ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ላይቶ ሚዲያን ለመጠቀም የስልጠናው አስፈላጊነቱ የላቀ ነው ።

ብልጽግና ፓርቲ ከተመሠረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ የውጭና የውስጥ ጫናዎችን በመቋቋም ያደሩ የትናንት የማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካ ዘርፍ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ኃላፊው አንስተዋል።

የተመዘገቡ ውጤቶች ለህዝቡ ተደራሽ እንዲሆኑ ስኬታማ የኮሙኒኬሽን ሥራዎችን ማጠናከር ይጠበቃል ያሉት አቶ ታከለ፤ የሚሰሩ ሥራዎች በህዝቡ ዘንድ ይሁንታ እንዳያገኝ የሚያደርጉ አስተሳሰቦችን መመከት፣ የፓርቲውን እና የመንግስት ስም ለማጥለሸት በዘመቻ የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመለየት እርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ተስፋነሽ ኢያሱ እንደገለፁት፤ ፓርቲው የሚሰራቸው ሥራዎችን ለይቶ በማወቅ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ ላይ ሁሉም የኮሙኒከተሪነት ሚናውን መወጣት ይገባል።

ከተቋም ባለፈ በግል ደረጃ ማህበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ ሁሉ ለህብረተሰቡ አዎንታዊ መረጃዎችን በማሰራጨት የመረጃ ተደራሽነት አድማሱን ማስፋት ይገባልም ብለዋል ወ/ሮ ተስፋነሽ ኢያሱ ።

” የድህረ እውነት ዘመን በእውነት እና በእውቀት” በሚል መሪ ቃል የተሰጠው ስልጠና የድህረ እውነት ዘመንን የፖለቲካ ኮሙኒከተሮች እንዴት መሻገር እንዳለባቸው ትልቅ አቅም የገነባ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የምዕራብ ኦሞ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበል ኢስያስ ናቸው።

የክልሉ አመራሮችና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደታች በማውረድ ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ ሚናቸውን መወጣት ይገባል ያሉት አቶ አበል፤ ብልጽግና ፓርቲ የሚሰሯቸው ሥራዎችን ለህዝቡ በተገቢው በማስገንዘብ የህዝብ ተሳትፎ የላቀ እንዲሆን በቁርጠኝነት መሥራት ከሁሉም ይጠበቃልም ብለዋል።

ዘመኑ በመረጃ ፍጥነት፣ጥራት እና ተደራሽነት በእጅጉ እየተወሳሰበ እየመጣ ባለበት ወቅት በመሆኑ የሚሰራጩ መረጃዎችን እውነትን ከውሸት በመለየት የህዝብን አንድነት በሚያጠናክሩ እና ሀገርን በሚያሻግሩ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ማዲያን ትውልድን በሚያነጽ መልኩ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት አቶ አበል ኢስያስ ያለንበት የአለማቀፋዊ ሁኔታዎችን ተረድቶ ሚዲያን መጠቀም ከብዙሃን የሚጠበቅ ነው ሲሉም ሀሳባቸውን ሰጥቷል ።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *