






የንግድና ኢንቨስትመንት ሴክተር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምስረታ ጀምሮ የእስካሁን ጉዞ እና የቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ዓላማ ያደረገ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነዉ።
በምክክር መድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤በሀገር ውስጥ የምናመርታቸው ምርቶችን በአይነት፣በብዛትና በጥራት ከፍ በማድረግ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማስቻል ይጠበቃል ብለዋል።
በክልሉ የኢንዱስትሪ ውጤቶች በጥቃቅንና አነስተኛ የማንፋክቸሪግ አማካኝነት እየተመረቱ ገበያውን የማረጋጋት ሥራቸው እያደገ መምጣቱን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በእንስሳት ሀብት ልማት የቁም እንስሳት ግብይት ከአካባቢ ገበያ አልፎ ለማዕከላዊ ገበያ የሚንቀሳስበት እድል እያደገ መምጣቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህም የቤተሰብ የኢኮኖሚ አቅምን የሚገነባና የአካባባቢውንና የክልሉን ለሀገር የኢኮኖሚ አቅም የሚያሳድግ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህንን ዘርፍ በተለየ ሁኔታ ቅንጅታዊ አሰራርን በማሳለጥ ውጤታማ እንዲሆን መደገፍና ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
በክልሉ ውስጥ የሚሰበሰበው ገቢ ከአመት አመት እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የገቢያችን ዋና ምንጭ የሆነው የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍን በየደረጃው ቀርብ ብሎ የሚያጋጥሙ የአሰራር ማነቆዎችን መፍታት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
የንግድ ፍቃድ ዕድሳትና ምዝገባ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በከተማና በገጠር ለኢንቨስትመንት የተሰጡ መሬቶችን በተገቢው በማልማትና በአግባቡ ኦዲት በማድረግ ወደ ልማት ያልገቡት ላይ እርምጃ መውሰድና ያልለሙ መሬቶችን ወደ መሬት ባንክ ማስመለስ ይጠበቃልም ብለዋል።
የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ በበኩላቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከክልል አልፎ ለሀገርና ለዓለም ገበያ የሚቀርብ የግብርና ፣የማዕድን እና ሌሎች እምቅ ሀብት ያለበት አከባቢ እንደሆነ ገልጸዋል።
ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ በንግድ ስርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት፣የንግድ ግብይት ሥርዓቱን ድጅታላይዝድ ለማድረግ እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማነቃቃትና አሰራሩን ለማሻሻል በክልሉ መንግስት ትኩረት ተደርጎ ሲሰራ ቆይቷል።
ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ በግብርና በኢንዲስትሪ እና በአገልግሎት በ364 ፕሮጀክቶች መግባታቸውንና ከክልሉ ምስረታ በፊት የነበረው 12 የነዳጅ ማደያ ወደ 33 እንዲደርሱ ሥራዎች መሰራታቸውንም አቶ ተመስገን ከበደ ጠቁመዋል።
በክልሉ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ መነቃቃት እየታዬ ቢሆንም ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፣የኤክስፖርት ምርት በብዛትና በጥራት በማምረት ለገበያ ማቅረብ፣የገበያ ትስስርና በሌሎች ጉዳዮች ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በመድረኩ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ ሌሎች የክልል፣የዞንና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ለምክክር መድረኩ መወያያ የተዘጋጀ ሰነድ እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን ከሚቀርበው ሰነድ መነሻ የጋራ ምክክር ይደረጋል።
በፍቅር ከበደ
