zCZ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ በክልሉ የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ የመከላከልና መቆጣጠር ስራዎችን በሚመለከት ከዞን ምክር ቤቶች አፌ-ጉባኤዎችና ከክልሉ ምክር ቤት የማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴዎች ጋር እየገመገመ ይገኛል።

በክልሉ የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፌ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ ይህንን ሚናቸውንም አጠናከረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የተከሰተውን የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የጤና ኤክስቴንሽን ስረዓትን በማጠናከር ጭምር የተጀመረው የተቀናጀ ተግባር የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ዋና አፌ-ጉባኤው በሁሉም መዋቅር ወጥነት ባለው አግባብ ወደ ተግባር ማስገባት በየደረጃው ካለው መዋቅር የሚጠበቅ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በወረርሽኙ መከላከል ተግባር የሚስተዋለው የመረጃ ጥራት መጓደል አሳሳቢ በመሆኑ በአፋጣኝ ማረም እንደሚገባ የገለጹት አቶ ወንድሙ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች ሚናቸውን በማጠናከር የወባ ወረርሽኝ መከላከል ተግባርን በተሟላ መልኩ መደገፍ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የህዝብ ምክር ቤቶች እና የክልሉ ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴዎች ወረርሽኙን በመከላከልና መቆጣጠሩ ሂዴት ከጤና ቢሮ ጋር በመተባበርና በቅንጅት በመስራታቸው በወረርሽኙ ልደርስ የሚችልን የከፋ ጉዳት መቀነስ መቻሉን የገለጹት የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ይህ መልካም ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።

ቢሮው የወባ መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም ህክምና ተግባርን በልዩ ትኩረት እየመራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኢብራሂም የክልሉ ምክር ቤት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት እያደረገ ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የቢሮው አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች በክልሉ ያደረጉትን ድጋፋዊ ክትትል ግብረ መልስ ለተሳታፊዎች እያቀረቡ የሚገኝ ሲሆን በሚቀርበው ዝርዝር ሪፖርት መነሻ ውይይት እንደሚደረግም ተግልጿል።

በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች፣ የዞን ምክር ቤት አፌ-ጉባኤዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *