




ቢሮው ከቦንጋ ዩኒቨርስቲ ጋር በመቀናጀት ለሰብልና ሆልቲ ካልቸር ባለሙያዎች በዘርፉ ስልጠና እየሰጠ ነው።
መገኛው በአሜሪካ እንደሆነ የሚነገርለት የአናናስ ሰብል ሞቃታማና አሲዳማ አፈር ላይ ሊተከል እንደሚችል የክልሉ ግብርና ቢሮ የእርሻና ሆልቲ ካልቸር ዘርፍ ኃላፊና ምክትል ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አሸናፊ ክንፉ ተናግረዋል ።
በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የክልሉን የማልማት አቅም የመለየት ስራ በስፋት መሰራቱንም አቶ አሸናፊ ተናግረዋል።
በክልሉ ሊለሙ ከሚችሉ ሰብሎች አናናስና ሙዝ ተጠቃሽ ሲሆኑ ለሰብሎቹ ተስማሚ ስነ ምህዳር መኖሩ ደግሞ ሰብሎቹን ለማልማት አመቺ ነው ሲሉም ተናግረዋል ።
በክልሉ ከ861 ሄክታር በላይ መሬት አሲዳማ መሆኑን የተናገሩት አቶ አሸናፊ የአናናስ ሰብልን በዚሁ መሬት ላይ በማልማት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶአደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በተሰራው ቅመራ ከፍተኛ ድርሻ የያዘው በክልሉ በጎጀብ እርሻ ልማት የአናናስ ሰብል መሆኑን የገለጹት አቶ አሸናፊ ምርቱን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በማልማት አርሶአደሩን ተጠቃሚ የማድረግ ኃላፊነትን አመራሩና ባለሙያዎች ወስደው መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
በክልሉ ከ3 ሺህ 500 በላይ ሄክታር በአናናስ ሰብል መሸፈኑንና በቀጣይ ግንቦት ወር ጀምሮ 1000 ሄክታር የአናናስ ሰብል ለመትከል ዕቅድ መያዙንም አቶ አሸናፊ ገልጸዋል።
ስልጠናው ለዘርፉ ባለሙያዎች እየተሰጠ ሲሆን በአናናስ አመራረት ፣ቅድመ ምርትና ድህረ ምርት አያያዝ ላይ በቦንጋ ዩኒቨርስቲ በአናናስ ሰብል ሲኒየር ተመራማሪ በሆኑት በአቶ አለሙ አንዷለም ተሰጥቷል።
የአናናስ ሰብል በዓለማችን ከሚመረቱ ከቆላ ፍራፍሬዎች ከሙዝና ማንጎ ቀጥሎ በ3ኛ ደረጃ የሚመረት ሲሆን 20 ከመቶ ድርሻ እንዳለውም አቶ አለሙ አንዷለም ገልጸዋል።
በሙዝ አመራረትና አያያዝ ቴክኖሎጂ ላይ ስልጠናውን የሰጡት የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ አቶ አሸናፊ አብርሃም የሙዝ ሰብል የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አልፎ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ገለጻ አድርገዋል።
በቦንጋ ዩኒቨርስቲ እየተሰጠ ያለው የአናናስና ሙዝ ፓኬጅ ስልጠና በክልሉ የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ድጋፍ ጋር በመተባበር ነው።
በታጠቅ አበበ
