



በከተማዋ ተጀመረው ኮሪደር ልማት ስራ ለዜጎችም ስራ ዕድል መፍጠሩ ተገልጿል ፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሚገኙ ከተሞች የከተማ ኮሪደር ልማት ስራዎች ተጠናክረው እየተሰሩ ይገኛል ፡፡
በቅርቡ ወደ ኮሪደር ልማት ስራ የገባው የታርጫ ከተማ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማጠናቀቅ ከአንድ ወር በፊት ስራውን በይፋ አስጀምሯል ፡፡
የተጀመረውን የኮሪደር ልማት ስራ ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ከአካባበው ነዋሪዎች ጋር በመግባባት እንደተጀመረ ከንቲባ ዳዊት ወንድሙ ተናግረዋል ፡፡
በዚህም ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣና መንግስት የሚጠበቅበትን ሁሉ በማከናወን ስራው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ እንደሚገንም አቶ ዳዊት አስረድተዋል ፡፡
እስከ አሁን ባለው ከህብረተሰቡ የጥሬ ገንዘብ ማሰባሰብ ስራው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰበሰበ እንደሚገንና አሁን ላይ ከ700 ሺህ ብር በላይ በመሰብሰብ ለዚሁ ዓላማ እንዲውል እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ዳዊት ተናግረዋል ፡፡
በኮሪደር ልማት ስራው ህዝብ መዝናና፣ የ1.05 ኪሎሜትር ከወጣቶች ማዕከል እስከ ታርጫ ሆስፒታል የመንገድ ዳር መብራት ዝርጋታ፣ ቴራዞ ንጣፍ፣የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ አረንጓዴ ስፍራዎችና የውሃ ፏፏቴ ስራዎች ኮሪደር ልማት ስራው አካል ሆነው እየተሰሩ ይገናልም ብለዋል ፡፡
በኮሪደር ልማት ስራው አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤታቸውን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው ስራዎች ለውጥ በማድረግ ገብያቸውን እንዲያሳድጉ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል ፡፡
ታርጫ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባቲሳ ወንድሙ በበኩላቸው ከተማው ለተለያዩ ኢንቨስትመንትና አገልግሎት ምቹ እንድትሆን ለማድረግ 10 ዓመቱን መሪ ዕቅድ መሰረት በማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
ከተማዋን ኮሪደር ልማት ስራ እውን ለማድረግ የወሰን ማስከበርና የሸራ ቤቶችን ማንሳት፣ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማተናከርና መሰል ተያያዥ ስራዎች ተጠናክረው እየተሰሩ መሆኑንም አቶ ባቲሳ ተናግረዋል ፡፡
አሁን ላይ በተጀመረው ኮሪደር ልማት ስራ ከ65 በላይ ለሆኑ ዜጎች ስራ ዕድል መፈጠሩንም አቶ ባቲሳ አስረድተዋል ፡፡
በታጠቅ አበበ
