የተፋሰስ ልማት ሥራ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በተጓዳኝ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጎላ ፋይዳ አለው – አቶ ማስረሻ በላቸው

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ የ2018 ዓ/ም የተቀናጀ የማኅበረሰብ አቀፍ የተፋሰስ ልማት ማብሰሪያ ፕሮግራም በምዕራብ ኦሞ ዞን፣ መኒት ጎልዲያ ወረዳ እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሐግብሩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፥ በክልሉ ከዚህ ቀደም በተከናወነው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በተጓዳኝ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጎላ ፋይዳ አለው ያሉት አቶ ማስረሻ፥ ኅብረተሰቡ በንቅናቄ ያሳየውን ተሳትፎ በማጠናከር በጥበቃና ስነ-ህይወታዊ ልማት ሥራ ላይ መድገም እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በ2018 ዓ/ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በክልሉ 1ሺህ 200 ነባርና አዲስ ንዑስ ተፋሰስ በማልማት 2መቶ 72 ሺህ ሄክታር መሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራን በሚቀጥሉት 45 ቀናት ለማከናወን በቂ ቅደም ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል።

“ዛሬ የምንሰራው የተፋሰስ ልማት ተግባር፣ ለነገው ትውልድ የውሃ ምንጭ፣ ለምና አረንጓዴ አካባቢ ዋስትና ነው” ነው ያሉት አቶ ማስረሻ ኅብረተሰቡ ይህንን ዘርፍ-ብዙ ጠቀሜታ በተገቢው በመገንዘብ የተፋሰስ ልማቱን ማከናወን አለበት ብለዋል።

የአርሶናአርብቶ አደር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግሥት ከገንዘብ አበዳሪ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የብድር አግልግሎት ለመስጠት እንቅስቃሴ መጀመሩን ያሳወቁት አቶ ማስረሻ፥ብሄራዊ መታወቂያን በማውጣት የብድሩ ተጠቃሚ መኾን እንደሚቻል ተናግረዋል።

ከተፋሰስ ልማት ሥራው ጎን ለጎን በየደረጃው የቡና ጉንደላና ነቀላ፣ የተፈጥሮ ማዳበርያ ዝግጅት፣ እንዲሁም ነባር ተፋሰሶች ላይ የስነ-ህይወታዊ ሥራዎች በልዩ ቁርጠኝነት ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዞኑ ከዚህ ቀደም በተከናወኑ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ምንጮችና ኩሬዎች ውሃ እያፈለቁ፣ የተራቆቱ መሬቶች እያገገሙ እንደኾነ የገለጹት የዞኑ ዋና አስተዳደር አቶ ታምሩ ቦኒ ተግባሩን በማጠናከር ተፈጥሮ ወደ ቀደመ መልኩ መመለስ ይገባል ብለዋል።

የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስትር ተወካይ አቶ ፋኖስ መኮንን በበኩላቸው እንደሀገር የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በልዩ ትኩረት እያከናወነ እንደኾነ በማንሳት በዚህም አውንታዊ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2018 ዓ/ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ 4.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚለማ መኾኑን የጠቆሙት አቶ ፋኖስ በዚህም ተግባር ከ25 ሚሊዮን በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *