51 ማሊዮን ችግኞችን በሴቶችና ህፃናት በማስተከል የአየር ንብረት ለውጥ እንድስተካከል የበኩላችንን ሚና እንወጣለን፦ወ/ሮ ገነት መኩሪያ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ “በመትከል እናሰራራለን ” በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ ያለው የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል የሆነውና ሴቶችና ህጻናት ብቻ የሚሳተፉበት “ኢትዮጵያ በሴቶችና ህፃናት አረንጓዴ ትለብሳለች” በሚል መሪ ቃል የአረንጓዴ አሻራ መርሀ -ግብር በቦንጋ መምህራን ኮሌጅ አከናውኗል።

በመርሀ-ግብሩ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ በዚህ መርሀ-ግብር 51ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን ተናግረዋል።

ወ/ሮ ገነት አክለውም በተያዘው ክረምት ሴት ባለሙያዎችም ሆኑ አመራሮች በያዙት የሙያ ዘርፎች ማለትም በጤና፣ በግብርና፣ በመምህርነት እና በተቀመጡ 14 ፓኬጆች መነሻ በተሰማሩበት የሙያ መስክ በተለያዩ ማህበራዊ ችግር ውስጥ ለገቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ነፃ አገልግሎት እንደሚሰጡም ገልፀዋል።

ችግኝ መትከል ብቻም ሳይሆን መንከባከብም እንደምያስፈልግ የተናገሩት ወ/ሮ ገነት በተያዘው ክረምት 14 ሚሊዮን ችግኞችንም ለመንከባከብ ዕቅድ እንደያዙም አስቀምጠዋል።

የካፋ ዞን ሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መዓዛ ኃ/ማሪያም በበኩላቸው እንደ ዞን 139 ሺ በሴቶች 37 ሺ ችግኞችን ህፃናት ለማስተከል አቅደው በተግባር ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

አክለውም በአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር የሚተከሉ ችግኞች የአየር ንብረትን ከመጠበቅ ባሻገር የምግብ ዋስትናን ልያረጋግጡ የምችሉ ችግኞችንም መትከል ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ እታለም ከበደ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ ተከላ ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ባሻገር ለወጣቶች የስራ ዕድል ልፈጥር እንደምችል እና ለሴቶችም ኢኮኖማያዊ ለውጥ ማና እንዳለው ጠቅሰዋል።

የቦንጋ ከተማ የሴቶች ህብረት አባል ወ/ሮ አባይነሽ አበበ በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር የሚተከሉ ችግኞች ለሴቶች ከሚፈጥሩት አቅም ይልቅ በአሁኑ ሰዓት አስቸጋሪ እየሆነ የሚመጣውን የመሬት መንሸራተት ልታደግ እንደምችል ገልፀው የተተከሉትንም ቢሆን እንደወለድናቸው ህፃናት በመንከባከብ ለውጥ ልናይባቸው ይገባናል ብለዋል።

የካፋ ዞን የህፃናት ፓርላማ አባል የሆነች ህፃን ማህደር ምትኩ የነገ ሀገር ተረካቢ እንደመሆናችን መጠን እየተተከሉ ያሉ ችግኞችን በማስቀጠልና በመንከባከብ አረንጓዴ አካባቢን በመፍጠር የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን ብለዋል።

በመርሀ-ግብሩ የካፋ ዞንና የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ሴት አመራሮች፣ ሴት የመንግስት ሠራተኞች፣ የሴቶች ልማት ህብረት አባላትና የቦንጋ ከተማ ሴትና ህጻናት ነዋሪዎች እንዲሁም የህፃናት ፓርላማ አባላት ተሳትፈዋል ሲል የካፋ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *