


ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በህብረት የተሳካ የኢትዮጵያ የማንሰራራት መገለጫ የይቻላል ማሳያም ጭምር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ በብዙ ልፋትና መስዋዕትነት የተገነባው ታላቁ የኢትዮጰያ ህዳሴ ግድብ በመስከረም ወር እንደሚመረቅ ማብሰራቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብ የጋራ ተጠቃሚነት አቋሟ የጸና መሆኑን መናገራቸውም እንዲሁ።
ኢዜአ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከማህበራዊ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ እውነቱ ሃይሉ(ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ እውነቱ ሃይሉ(ዶ/ር) እንደሚሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአንድነት ታሪክ መስራት እንደሚቻል ምልክት ነው።
ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ሃብት፣ እውቀትና ጉልበት በትብብር የተገነባ ትውልድ ተሻጋሪ ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ በአንድነት በመቆም ዛሬም ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ለአለም ያሳዩበት እንደሆነም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት የሚያስችል የምጣኔ ሃብት አቅም የላትም በተባለበት ወቅት በአንድነት ታሪክ መስራት እንደሚችል በተግባር ማስመስከር ተችሏል ነው ያሉት።
በሀገራቸው ጉዳይ በአንድነት የሚሰለፉት ኢትዮጵያውያን ድህነትን ለማሸነፍ እውቀት፣ ገንዘብና ጉልበት ተደምሮ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በህዳሴ ግድብ አሳይተዋል ብለዋል።
ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን ብርሃን፣ ጉልበት፣ የአንድነት ምልክት እንዲሁም በትብብር ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ለአለም ያሳዩበት እንደሆነም ተመራማሪው ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
