
መንግስት ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት እና የህዝቦችን ሁለንተናዊ ፍላጎቶች ለመድረስ ከተለያዩ ምንጮች የተገኘውን ሀብት በኃላፊነትና ተጠያቂት ስሜት ለህዝቡ ማድረስ የሚችል የፋይንስ አሠራር ስርዓትን ለመዘርጋት ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንዳለ ይገለጻል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተመሠረተ ወዲህ ሀገራዊ የአሰራር ማሻሻያዎችን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ አዋጆችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በማውጣት ከዚህ ቀደም ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን ለማረም የተከደበት እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ከተከናወኑ ውይይቶችና ጉባኤያት መገንዘብ ተችሏል።
በዛሬው ዝግጅታችን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊዋ ጋር የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና 2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ያደረግነውን ውይይት እንደሚከተለው አቅርበናል።
መልካም ንባብ!
መ/ኮ: ለቃለ-መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ አመሰግናለሁ፤ ራስዎትን ያስተዋውቁና ወደ ጉዳዩ እንግባ
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- እነም አመሰግናለሁ፤ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ እባላለሁ፣ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ነኝ፡፡
መ/ኮ: ሀገራዊ የፋይናንስ ተቋም ሪፎርም በክልላችን እንዴት እየተተገበረ ነው? ውጤቱንስ እንዴት ያዩታል?
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- እንደ ሀገር ሪፎርም ካስፈለጋቸው ተቋማት አንዱ እና ቀዳሚው የፋይናንስ ሴክተር መሆኑ ይታወቃል። በዚህም መንግስት ወጥ እና ሀገር አቀፍ አሰራሮችን የያዘ የህግ ማዕቀፎችን አርቅቆ በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመዘርጋት ብዙ ስራዎች ሰርቷል።
ይህን ተከትሎ በክልላችንም ሀገራዊ አሠራሮችን በመተግበር ጠንካራ የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓትን ለመዘርጋት ቅንጅታዊ ስራዎች ተሰርቷል፤ በዚህም ግልጽ፣ ዘመናዊና ውጤታማ አሰራር እንዲዘረጋ የክልሉ መንግስትና ባለድርሻ አካላት ትኩረት ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል።
መ/ኮ:- የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እንዴት ይገለጻል?
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ታቅደው የተገቡ ተቋማዊ የማስፈፀም ብቃትን በማስቀደም የፋይናንስ ሥርዓቱን በተለያዩ ማዕቀፎች በማደራጀት የተጀመረው ስራ ያመጣውን ውጤት ለመፈተሽ ጉባኤ አዘጋጅተን ገምግመናል።
በጉባኤውም በተለያዩ ጊዜያት እንደቃኘነውም በጣም ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት የበጀት ዓመት ነበር። በ2017 ውጤት ተመዘገበ ስንል በደፈናው ሳይሆን በየዘርፉ ያስቀመጥናቸውን ግቦች ቆጥረን በማየት ሲሆን፤ አሁንም ብዙ መሻሻሎች የሚያስፈልጋቸውን ነጥቦች ሳንዘነጋ ጠቅላላ ተግባራትን በማየት ነው።
መ/ኮ: ውጤት ተመዘገበ ካሉ ምን ምን ላይ እንደሆነ ብያብራሩ
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- ከበጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በተለያዩ ወጪ አርዕስቶች የተመደበውን በጀት በአግባቡ በመደልደል ወደ ስራ ገብተን ከወትሮ በተለየ ትኩረት ቅድሚያ መስጠት ላለብን አስገዳጅ ወጪዎችና ሰብዓዊ አገልግሎት ክፍያዎች ማለትም ደሞዝ ላይ የበጀት እጥረት እንዳይከሰት በማድረግ አገባድደናል።
እነዚህ ዘርፎች አብዛኛውን የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን ይፈጥሩ የነበሩ ሲሆን ዛሬ ላይ በዝህ አኳኃን ማየታችን ይበል የሚያሰኝ ነው። ከዝህም በተጨማሪ ተቋማዊ የማስፈፀም አቅም እየተሻሻለ የመጣበት እና የውስጥ ኦዲት ስርዓቱ የተጠናከረበት በጀት ዓመት መሆኑንም አይተናል።
መ/ኮ:- በክልላችን አንድ አንድ መዋቅሮች ላይ ከሰብዓዊ ክፍያዊች ጋር ተያይዘው የደመወዝ መዘግየት ቅሬታዎች ይነሱ ነበርና በ2017 በጀት ዓመት ምን የተለየ ስራ ሰርታችኋል፣ ለቀጣይስ መሰል ችግር እንዳይሰማ ምን ታስበዋል?
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- ከዚህ ቀደም በየመዋቅሮቹ ስናይ የውስጥ ገቢ ይሰበሰብና የወጪ አስተዳደር ስርዓቱን የሚመራበት መንገድ መስተካከል እንዳለበት ተገምግመው ከድጎማ በጀት ይልቅ የውስጥ አቅም በማጠናከር ላይ እንደ ክልል የወሰድነው የመፍትሔ አቅጣጫ ዛሬ ላይ መሻሻል አሳይቷል።
ባሳለፍነው በጀት ዓመት በመንግስት እስትራቴጂ መሠረት የተሻሻሉ የበጀት አጠቃቀም መመሪያዎችን እውን በማድረግ ሰብዓዊ ክፍያዎች ከቀደሙ በኃላ ሌሎች ድህነት ተኮር መስርያ ቤቶች ማለትም አጠቃላይ የመሠረተ ልማት ተቋማት ደረጃውን የጠበቀ በጀት እንዲመደብ እና እንዲተገበር በማድረጋችን ነው።
ከዚህ በተጨማሪ 60/40 ሬሽዮ ማለትም 60% ለድህነት ቀናሽ ተቋማትና 40% ለአስተዳደራዊና ግዴታ ወጪዎች ባሉባቸው ተቋማት ላይ በማድረግ አስፈፅመናል። የሚሰበሰቡ ገቢዎች አላግባብ እንዳይባክኑ የወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ስርዓቱን በማጠናከር መመርያ በማውረድ አላስፈለሰጊ ወይንም አንገብጋቢ ያልሆኑ ወጪዎች እንዳይፈፀሙ ድጋፍና ክትትል ተደርገዋል።
መ/ኮ:- ለጠቅላላ አፈጻጸማችሁ የተከተላችሁ ተቋማዊ እስትራቴጂ ካለ ብገልፁልን
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- ከላይ የተገለፁትን ውጤት ለማምጣት የተለያዩ ጥረቶችን አድርገናል፣ ወደ ዞኖችም ስንኸድ የወጪ አስተዳደር ስርዓቱን እና የገቢ ሚዛኑን ማስተካከል ስለነበረብን የገቢ ጉዳይ ላይ ልዩ አፅንኦት መስጠታችን ለተሻለ አፈጻጸም አድርሶናል።
ሌላኛው ወሳኝ ነገር የውስጥ ቁጥጥር ስርዓትን በማጠናከር እያንዳንዱ የፋይናንስ ተቋም ወጪዎችን ስያስተዳድር የትኛው ነው አስገዳጅ? የቱ ለምን እና እንዴት ተፈቀደ? የሚሉትን ጉዳዮች ትኩረት በማድግ ቅድም ያነሳሁት የበጀት ርዕሶች በትክክል መፈጸማቸውን የውስጥ ኦዲት ስርዓቱን በማጠናከር የድጋፍና ክትትል ስራ ሰርተናል። ከዚህም አንፃር የተሻለ አፈጻጸም ቢመዘገብም ወደፊት ጠንክረን መስራት ያለብን ጉዳይ መሆኑን ገምግመናል።
መ/ኮ:- ከኦዲት ግኝት ጋር ተያይዘው ግኝቶችን የማስመለስ ጉደይ እንዴት ያዩታል? ከዝህ የተሻለ ለመስራት ምን ታቅደዋል?
ወ/ሮ ወሰነች:- በጀት ከተዘጋ በኃላ በክልሉ ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ኦዲት ይደረጋል። በዚህም ከ 2013 በጀት ዓመት ጀምሮ እስከ 2016 በጀት ዓመት ድረስ ከክልል ተቋማት እስከ ወረዳ ድረስ የተመዘገቡ የኦዲት ግኝቶች አሉ። እነዝህ ግኝቶች: ግኝት ብቻ ሆኖ እንዳይቀመጡ በፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ተመላሽ እንድሆኑ ተደርገዋል።
ከዚህ ቀደም የግኝት አመላለስ አፈጻጸማችን ደካማ (6%) ነበር ፣ በ2017 በጀት ዓመት በዋና አፈጉባኤ የሚመራ እና ፋይናንስ ቢሮ አባል የነበረበት ክልላዊ ግብረ ኃይል ልዩ ትኩረት በማድረግ እስከ ታችኞቹ መዋቅሮች በመውረድ በግለሰቦች እጅ እየባከነ ያለውን የመንግስት ሀብት እንድሁም ያልተስተካከሉ አሰራሮችን በማሳረም ከነበረበት 6% ወደ 70% ማድረስ ተችሏል። ይኸውም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለበትና የግኝት አመላለስ 0 % እስክሆን መስራት እንዳለብን መግባባት ላይ ደርሰናል።
በቀጣይ ዓመትም ግኝት አመላለስን ዜሮ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ግኝት እንዳይኖር የውስጥ ቁጥጥር ስራዓትን በማጠናከር፣ የውስጥ ኦዲተሮች አቅም በማጎልበት ዜሮ ግኝት እንዲሆን መስራት ይጠበቅናል።
መ/ኮ:- የህብረተሰባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የፋይናንስ ስርዓትን ከማጠናከር ባሻገር ምን የተለየ ስራ ተሠርቷል?
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- በክልሉ ሁሉንተናዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት የገቢ አቅምን በብዙ እጥፍ መጨመር ስለነበረብን በክልል ስንደራጅ መጀመረያ ላይ የነበረው ክልላዊ ገቢ 2.4 ቢልዮን ነበር፤ አሁን ባሳለፍነው በ 2017 በጀት ዓመት ወደ 9.66 ቢልዮን አድርሰናል። ስለዚህ የውስጥ ገቢን በዝህ ሁኔታ ማሳደግ ከቻልን የመሠረት ልማት፣ መልካም አስተዳደር እና ሰብዓዊ ክፍያ ጥያቄ የማይመለስበት ምክንያት አይኖርም ማለት ነው።
መ/ኮ:- የገቢ እና ወጪ አስተዳደርን በተመለከተ በቅርቡ በመስተደደር ምክር ቤት የወጣው ደንብ ቁጥር 46/2017 ምን የተለየ አስተዋፅኦ ይኖረዋል?
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- የሚሰበሰበውን ገቢ በአግባቡ ለማስተዳደር በመስተዳደር ምክር ቤት ትኩረት ተሰጥተው የገቢ አሰባሰብና አጠቃቀም መመርያ (ደንብ 46/2017) ወጥቷል።
ይህም ደንብ ከዝህ ቀደም የወጪ አስተዳደር ስርዓቱን ሲያስተጓጉል የነበረውን አሠራር የሚያስቀር ሲሆን በየመዋቅሮች የሚሰበሰበውን ገቢ በአንድ ዝግና ልዩ አካወንት በማድረግ በወር አንዴ ብቻ ለሰብዓዊ ወጪና አስገዳጅ ወጪዎች ቅድሚያ በመስጠት ሌሎችን የሚያስከትል የወጪ አስተደዳር ስርዓትን የሚያሰፍን በመሆኑ ተስፋ ተጥሎበታል። ለአፈጻጸሙም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገን መግባባቶችን ፈጥረናል፤ ይህ ደንብ ብዙ ጊዜ በተለያዩ መዋቅሮች ላይ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ይቀርፋል ብለን እናምናለን።
መ/ኮ: በመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚፈፀሙ አንዳንድ ግዥዎች ከወቅቱ ገበያ ጋር ያለመጣጣሙ የሚፈጥረውን የአሰራር ጫናዎችን ለመፍታት ምን አቀዳችሁ?
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- እንደ ሠራተኞች ደንብ ልብስ አጠቃቀምና አፈጻጸም እና መሰል ግዥዎች የራሳቸው የሆነ መመሪያ ያለው ቢሆንም አሁን እያደገ የመጣውን ገበያ መሸከም እየቻለ ባለመሆኑ እንደ ክልል ከፐብሊክ ሠርቪስ ጋር በመቀናጀት እየታየ ያለውን ጫና ለመቀነስ የምንሰራ ይሆናል። እስካሁን ግን በነባሩ በመመሪያ እየተመራን ነው።
መ/ኮ:- ከግዥ ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ጥሰቶችን ለማረም ምን የተለየ እቅድ አላችሁ፤ ከጨረታ በኃላ በዋጋ ግሽበት ስም የሚፈጠረውንስ ማጉላላት ለመቀነስ ምን ታስበዋል?
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- የግዥ ስርዓቶች አፈጻጸም በተመለከተ በሀገራዊ አዋጅ መሠረት የረቀቀውን መመሪያ ተከትለን ህደቶችን እያስፈፀምን ነው። ከግዥ ጋር ተያይዘው ለሚነሱት ቅሬታዎች ለግዥ ፈጻሚ ተቋሞቻችን እና ተሳታፊ የንግዱ ማህበረሰብ ተጨማሪ ስልጠና ለመስጠትና የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓቱን ለመተግበር የሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ለመስራት አቅደናል።
ሌላኛው የግዥ ህደቶችን የሚያደናቅፈው የጨረታ ሂደቶችን ጨርሰው ካሸነፉ በኃላ ግዥዎች እንዳይፈጸሙ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ሲሆኑ፤ ለዝህም ቀደም ብለው እንደተገለፀው ለሁለም ባለድርሻ ግንዛቤ የሚሰጥ ሲሆን ማንኛውም የግዥ ሰነድ እስታንዳርዱን የጠበቁ ስለሆኑ አጽዳቂ ኮሚቴዎች በኃላፊነት እንዲሰሩና ማንኛውም ተጫራች ዝርዝር መጠየቆችን ተከትለው እስካሸነፈ ድረስ የገበያ እጥረት ገጥሞኛል ብለው መቅረብ እንደማይችል የግንዛቤ እንድሁም የተጠያቂነት ስርዓትን ለማስፈን የሚንሰራ ይሆናል።
መ/ኮ:- ከ2018 በጀት ዓመት ዕቅዶች ላይ የሚናገሩት ጉዳይ ካለዎት እንድሁም የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለዎት
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- የ2018 ዕቅዶቻችን በዋናነት 2017 ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ያደሩ ተግባራት ላይ ትኩረት አደርገን በቀጣይ በጀት ዓመትም ሀገራዊ ዕቅድን መሠረት በማድረግ በሁሉም የትኩረት መስኮቻችን ነጥቦችን ለይተን አስቀምጠናል። እነዚያን ተግባራት ለመፈጸምም አስቻይ ሁኔታዎች እንዳሉ ተመልክተናል። ሁሉም ዕቅዶቻችን ተቋማዊና ከታችኞቹ መዋቅሮች የሚጀምሩ ስለሆኑ የተናበበ እንዲሆን ሁሉም በትጋት እንዲሰራ እና ወቅቱ በጀት የሚደለደልበት ጊዜ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በየምክር ቤቶቻቸው በጊዜ በማፅደቅ ተባባሪ እና ፈፃሚ እንዲሆኑ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
መ/ኮ:- በተነሱት ነጥቦች ላይ ለሰጡት ማብራሪያ እጅግ አመሠግናለሁ!
ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ:- እኔም አመሠግናለሁ።
በአሻግሬ ገ/ወልድ
