በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የብልጽግና ፓርቲ የልዑካን ቡድን በቻይና የተለያዩ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም የሚያስችል ጉብኝት አደረገ

Spread the love

በብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ የሚመራው የፓርቲው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በቻይና የተለያዩ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም የሚያስችል ጉብኝት አደረገ።

ቡድኑ በግብርና ምርት ከፍተኛ ውጤት እያገኘች ባለችው ኽናን ግዛት በመገኘት በግብርና ምርታማነት፣ በኢንዱስትሪ፣ በሲቪል አቪዬሽን፣ በገጠር መንደሮች ልማትና በቅርስ፣ ባህልና ታሪክ ጥበቃ እየተከናወኑ ያሉ ውጤታማ ተግባራትን ጎብኝቷል።

ቡድኑ በጉብኝቱ በግብርና መስክ በተደረጉ ውጤታማ ስራዎች ግዛቷ የቻይናን ግማሽ ያህል የስንዴ ምርት እንዲሁም ሌሎች የጥራጥሬ ምርቶችን ማምረት እና በዚህም ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገቧን እንደተመለከተ ተገልጿል።

ከግብርና ባሻገርም በኢንዱስትሪ መስክ ሰፋፊ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሀገሪቱ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን፣ እነዚህን ምርቶች ወደ ተቀረው የቻይና ክፍል እንዲሁም ወደ መላው ዓለም ለማዳረስ የተሻለ የመሰረተ ልማት ግንባታ ባለቤት መሆኗንም የልኡካን ቡድኑ ተመልክቷል።

የገጠር መንደሮች ያላቸውን ልዩ እምቅ አቅም አቀናጅተው በመጠቀምና ማህበረሰቡን በማስተባበር ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግና ዘላቂ የስራ እድል ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ውጤታማ ስራዎች የልኡካን ቡድኑ ከጎበኛቸው ስራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በመስክ ጎበኝቱ ወቅት የታየው ሌላው መልካም ተሞክሮ በሲቪል አቪዬሽን መስክ የተፈጠረው አቅም ሲሆን በተለይም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር የተፈጠረውን የጭነት (ካርጎ) ትብብርና ትብብሩን ለማሳደግ እየተከናወኑ ባሉ ሥራዎች ዙሪያ ለልዑካን ቡድኑ ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንደቀረበለትም ተገልጿል።

ከግዛቷ አመራሮች ጋር በተደረገ ውይይትም አቶ አደም ፋራህ በግብርና ልማትና ሜካናይዜሽን እድገት፣ በቡና ኤክስፖርትና ፕሮሰሲንግ አቅም፣ በሲቪል አቪዬሽንና ቴክኖሎጂ መስኮች ያለውን ትብብር ማሳደግ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የግዛቷ አመራሮችም የተነሱትን ሀሳቦች በአድናቆት መቀበላቸውን እና የበኩላቸውን ሚና ለመውጣት ዝግጁ መሆናቸውን ቃል ገብተዋል።

የልዑካን ቡድኑ በአጠቃላይ በቻይና ሲያደርገው የነበረውን የተሞክሮ ልውውጥ ቆይታ አጠናቆ ዛሬ ማለዳ ወደ ሀገር ተመልሷል።

የልዑካን ቡድኑ ከአቶ አደም ፋራህ በተጨማሪ የአደረጃጀት፣ የፖለቲካ ባህል ግንባታ፣ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የስትራቴጂ እቅድ ዘርፍ ኃላፊዎች፤ የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ሐረሪ፣ ሲዳማ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፤ የፖለቲካ፣ የጥናትና ምርምር እና የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ዘርፍ ኃላፊዎች እንዲሁም የሴቶች ሊግ ምክትል ፕሬዝዳንትና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ልዩ ረዳትን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *