



በዳውሮ ዞን ለረዥም ዓመታት የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የነበረው የወልደሀነ-ዱርጊ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ መጀመር እንዲሁም የታርጫ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመርቀው ለአግልግሎት መብቃቱ እንዳስደሰታቸው ያነጋገርናቸው የአከባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
በዳውሮ ዞን የገና እና የዛባ ወረዳዎች ከአጎራባች የካምባታ እና ጣምባሮ አከባቢዎች ጋር ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ጠንካራ ማህበራዊና ኢኮኖሚ ትስስር እንዳላቸው ያነሱት የአከባቢው ነዋሪ ከሆኑት መካከል ቄሲስ መኩሪያ መለስ እና አቶ አገኖ አቱሞ ይኸው የህዝብ ጥያቄ ተጠናክሮ በመምጣት በ2010 ዓ/ም መላው የዞኑ ነዋሪዎች የመንገድ ከፈታውን በእጅ ለመስራት እንቅስቃሴ ያደረጉት ታሪካዊና ግንባር ቀደም የህዝቡ የልማት ጥያቄ መሆኑን አውስተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ እና ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝቡ የረዥም ዓመታት የልማት ጥያቄ ፈጣንና ቀልጣፋ ምላሽ መሰጠቱ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው በዚህም ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
የመንገድ ግንባታ ሁለቱን ክልሎች እንዲሁም የጅማ ዞን አከባቢዎችን በአንድ የሚያስተሳስር የጎላ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን በመግለጽ ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ ለአግልግሎት እንዲበቃ የአከባቢው ነዋሪዎች ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
መንገዱ የሚገነባበት ቦታ በአብዛኛው የመንግሥት የወል መሬት በመሆኑ ከወሰን ማስከበርና ተያያዥ ጉዳዮች የሚጠፋ ጊዜ አይኖረውም ያሉት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ወንድሙ ወጁ የመንገድ ግንባታው እውን መሆን ጥልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
የታርጫ ከተማ ከተቆረቆረች ጊዜ አንስተው በከተማው የሚስተዋለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር በአስተማማኝ ደረጃ የሚቀርፍ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ እንዳስደሰታቸው የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በከተማው የታኪስ መንደር ነዋሪ ከሆኑት መካከል ትዕግስት ብላቴ እና ኤልሳቤጥ አድማሱ የታርጫ ከተማ ውሃ ስርጭት አስተማማኝ ባለመሆኑ ለረዥም ወራት ውሃ ማግኘት የማይቻል እንደነበረ በመግለጽ የውሃ ፍጆታን በከተማው አቅራቢያ ከሚገኘው ሻታ ወራጅ ውሃ ላይ መሠረት ያደረገ እንደነበረና በዚህም ደህንነትና ጤንነት ባልጠበቅ ውሃ ህብረተሰቡ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ እንደነበረ አንስተዋል።
አሁን ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ባለው የውሃ ፕሮጀክት ንጹሕ ውሃን አስተማማኝ በሆነ መልኩ እያገኙ እንደሆነ ተናግረው መንግሥት ለታርጫ ከተማ የውሃ ችግር የሰጠው ምላሽ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ ተጠቃሚው ህብረተሰብ የውሃ መሠረተ ልማት በመጠበቅና ጉዳት እንዳይደርስበት በማድረግ ዘላቂና አስተማማኝ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲኖር ሁሉም ተጠቃሚ በባለቤትነት መጠቀም እንዳለበት አሳስበዋል።
በዕድገቱ በዛብህ
