




የፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከወከላቸው ህዝብ ጋር ያደረጉት የውይይት ግብረ-መልስ ለክልሉ ካቢኔ አካላት በቦንጋ ከተማ አቅርበዋል።
በመድረኩ በክልሉ የተጀመሩ የሠላምና ፀጥታ ንቅናቄ መድረኮች ውጤታማ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተመልክቷል ፡፡
በክልሉ የጤናና የውሃ ፕሮጀክቶችን ለማንቀሳቀስ እና በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ ለመጨረስ የሚደረገው ጥረት እጅግ አበረታች መሆኑ ተገልጿል፡፡
የተጀመሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም አኳያ ጥሩ መነቃቃት ስለመኖሩ፣ ሌብነትና ብልሹ አሠራርን ለማረም እየተደረገ ያለው ተግባር መጠናከር እንዳለበት የተነሳ ሲሆን የህዝብ ተሳትፎ ከጤናና ትምህርት ተግባራት አንፃር መልካም ጅምሮች እንዳሉ በግብረ መልሱ ተመልክቷል ፡፡
በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማት ትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ እሸቱ ገ/ማሪያም ግብረ-መልሱን ለመድረኩ አቅርበዋል።
በዚሁ ወቅትም ምክር ቤት አባላት ዋና ተግባራቸው የወከላቸው የህዝብ ውክልና ማረጋገጥ በመሆኑ የምክር ቤት አባላት በክልሉ ከመረጣቸው ህዝብ ጋር በሰላምና ፀጥታ፣ ኢኮኖሚ ልማት፣ ማህበራዊ ጉዳዮች እና መሠረተ ልማት አቅርቦትና አገልግሎት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ገልጸዋል።
በመድረኩ በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ ጥያቄዎችን በመደመመጥ፣ በመከባበርና በመመካከር በመፍታት የተረጋጋ የፖለቲካ ስነ- ምህደር መፍጠር መቻሉን ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ ገልጸዋል።
በመንገድና ድልድይ ግንባታ፣የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ትምህርትና ጤና እንዲሁም ከወጣቶች ስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየታቸዉን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
በክልሉ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት አንፃር የተጀመሩ 10 ግንባታዎች እንደሉና የተወሰኑትን በተያዘው በጀት አመት ለማጠናቀቅ በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከትምህርት ጥረት አንፃር የመምህራን አቅም ለመጠቀም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለው ፀጥታን ለማረጋገጥ የተለያዩ ውይይቶችን በማድረግ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሉም ጠቁመዋል፡፡
ያሉት የፀጥታ ሁኔታን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በአንዳንድ አካባቢዎች አሁንም ተጨማሪ የፀጥታ ኃይል የማሰመራት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
በግብረ-መልስ በተነሱ ነጥቦች ላይ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ስጥተዋል።
ከሠላምና ፀጥታ አንፃር የክልሉ ሠላም ለማስፈን ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑና አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት በክልሉ ዘላቂ ሠላም ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ እና ይህንንም ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ ህዝባዊ ውይይቶች እየተደረጉ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡
በክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት 40 ከመቶ ማድረስ የተቻለ ሲሆን የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በጥሩ ደረጀ ላይ እንዳሉ ተገልጾ፤ በውሃ አቅርቦት የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጡትን ቦታዎች በመለየት በትኩረት እንደሚሰራም ተገልጿል፡፡
በጤና የወባና ኩፍኝ ውራርሽኝ ለመከላከል ሰፊ ስራዎች እየተሰራ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በክልሉ የጤና ጣቢያ ግንባታ ሽፋን ለማሳደግ ብርቱ ጥረት እንደሚያስፈልግ የተቀዛቀዘውን የጤና ኤክስቴንሽን ስራ ለማጠናከር ጅምር ስራዎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት እንዲጠናከር መስራት ይገባል ተብሏል።
ከትምህርት ስራ አኳያ ተማሪዎች መጽሔት ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ የመጽሐፍ ህትመት ላይ በፍጥነት በመረባረብ ለማጠናቀቅ የሚሰራ እንደሆነና በክልሉ 1.4 ሚሊየን ሁለተኛ ደረጀ ትምህርት ቤት መጽሐፍ ተደራሽ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን በአርብቶ አደር አካባቢ ሞዴል ትምህርት ቤቶች ግንባታ በትኩረት ይሰራል ተብሏል።
በግብረመልስ በተነሱ ነጥቦች ላይ ውይይት ተደርጎ ክልሉ ድጋፍ በሚሻባቸው ጉዳዮች ለፌዴራል ፓርላማ ተወካይ ምክር ቤት አባላት ቀርቦ መድረኩ ተጠናቋል፡፡
በተከተል ወ/ሚካኤል
