



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ከክልሉ የስፖርት ፌዴሬሽኖች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አመራሮች፣ የክልሉ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ፕረዚዳንቶችና ምክትል ፕረዚዳንቶች፣ የባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊዎች፣ የዞን ፋሲሊቲና አደረጃጀት ሥራ ሂደት ቡድን መሪዎች፣ የቢሮ የስፖርት ዘርፍ ዳይሬክተሮች፣ ባለሙያዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የምክክር መድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮ ምክትል ሃላፊና የስፖርት ዘርፍ ሃላፊ አቶ አህመዲን አወል ስፖርት ከመዝናኛነት ባሻገር ለልማት፣ ለአንድነት እና ለሠላም ግንባታ ያለው ፋይዳው ትልቅ እንደሆነ በማንሳት በስፖርት ዘርፍ የሚታየውን ውስንነቶች በመቅረፍ ውጤት ማስመዝገብ አስፈላጊ እንደሆነ አንስተዋል።
አክለውም ስፖርትን ህዝባዊ መሠረት ከማስያዝ አንፃር የሚታዩ ጉድለቶችን በማረም ስፖርት ህዝባዊ እንዲሆን ጠንካራ ሥራ መስራት አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል። በዋናነት ስፖርት ሲነሳ መነሳት ያለበት የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ባለቤትነት፣ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ፕሮጀክት፣ የስፖርት ማህበራት፣ የስፖርት ምክርቤቶች፣ ፌዴሬሽኖች እና የስፖርት ገቢ ልዩ ትኩረት መሰጠት የሚገቡ ተግባራት መሆኑን አብራርተዋል።
አያይዘው በክልሉ ውስጥ 13 የስፖርት ፌዴሬሽኖች ምስረታ ጉባኤ ተካሄዶ ሥራ ውስጥ እንደገቡ በማንሳት በቀጣይ 4 የስፖርት ፌዴሬሽኖች ምስረታ ለማካሄድ ቢሮ ዕቅድ እንዳለው ተናግሯል።
በፌዴሬሽኖች በኩል የተሰሩ ስራዎች ውስንነት መኖሩን በማንሳት በዚህ ሂደትም የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉ እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ባህል ስፖርት፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ዉሹ፣ እጅ ኳስ እና ጅምናስቲ ፌዴሬሽኖች መኖራቸው በአብነት መጠቀሱን የቢሮዉ መረጃ ያመለክታል።
